ሪያል ማድሪድ እና አል ሂላል ወደ ጥሎ ማለፉ ገብተዋል - ኢዜአ አማርኛ
ሪያል ማድሪድ እና አል ሂላል ወደ ጥሎ ማለፉ ገብተዋል

አዲስ አበባ ፤ ሰኔ 20/2017(ኢዜአ)፦ በፊፋ የክለቦች ዓለም ዋንጫ የምድብ ስምንት የመጨረሻ ጨዋታዎች ትናንት ከእኩለ ሌሊት በኋላ ተካሂደዋል።
በሊንከን ፋይናንሻል ፊልድ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ሪያል ማድሪድ ሳልስበርግን 3 ለ 0 አሸንፏል።
ቪኒሺየስ ጁኒየር፣ ፌዴሪኮ ቫልቬርዴ እና ጎንዛሎ ጋርሺያ ግቦቹን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።
ውጤቱን ተከትሎ ሪያል ማድሪድ በሰባት ነጥብ የምድቡ መሪ በመሆን ወደ ጥሎ ማለፉ ገብቷል።
ሳልስበርግ በአራት ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዞ ከውድድሩ ተሰናብቷል።
በዚሁ ምድብ በጂኦዲስ ፓርክ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ አል ሂላል ፓቹካን 2 ለ 0 አሸንፏል።
ሳሌም አል-ዶውሳሪ እና ማርኮስ ሊኦናርዶ ግቦቹን አስቆጥረዋል።
አል-ሂላል በአምስት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ጥሎ ማለፉን ተቀላቅሏል።
በምድቡ ሶስተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ፓቹካ ያለ ምንም ነጥብ የመጨረሻውን አራተኛ ደረጃ ይዟል።
ጨዋታዎቹን ተከትሎ የምድብ ጨዋታዎች ፍጻሜ አግኝተዋል።
ሪያል ማድሪድ ከጁቬንቱስ፣ ማንችስተር ሲቲ ከአል ሂላል በጥሎ ማለፉ ይገናኛሉ።
የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ከነገ ጀምሮ ይካሄዳሉ።