ሃይደር ሸረፋ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ኮከብ ተጫዋች ሆኖ ተመረጠ - ኢዜአ አማርኛ
ሃይደር ሸረፋ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ኮከብ ተጫዋች ሆኖ ተመረጠ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 19/2017 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ መድን የአማካይ ተጫዋች ሃይደር ሸረፋ የ2017 ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ኮከብ ተጫዋች ሆኖ ተመርጧል።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ስሑል ሽሬ እና ኢትዮጵያ መድን ባደረጉት ጨዋታ ፍጻሜውን አግኝቷል።
ከጨዋታው በኋላ የ2017 የኮከቦች ሽልማት ስነ ስርዓት ተካሄዷል።
በዚሁ መሰረት የኢትዮጵያ መድን የአማካይ ተጫዋች ሃይደር ሸረፋ የዓመቱ ኮከብ ተጫዋች ሽልማትን አግኝቷል። የ210 ሺህ ብር ሽልማትም ተበርክቶለታል።
የሃዋሳ ከተማው አጥቂ ዓሊ ሱሌይማን በ21 ግቦች የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ በመሆን የ200 ሺህ ብር ሽልማት አግኝቷል።
ዓሊ ሱሌይማን በ2016 የውድድር ዓመትም በ20 ግቦች የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ እንደነበር የሚታወስ ነው።
የኢትዮጵያ መድኑ አቡበከር ኑራ ኮከብ ግብ ጠባቂ እና የኢትዮጵያ መድኑ ገብረመድህን ኃይሌ ኮከብ አሰልጣኝ በመሆን በተመሳሳይ የ200 ሺህ ብር ሽልማት አግኝተዋል።
ኮከብ ተስፈኛ ተጫዋች ሆኖ የተመረጠው የኢትዮጵያ ቡናው ይታገሱ ታሪኩ 105 ሺህ ብር ተሸልሟል።
ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ማኑኤ ወልደፃዲቅ የዓመቱ ምስጉን ዋና ዳኛ ሆነው የተመረጡ ሲሆን የ150 ሺህ ብር ተሸላሚ ሆነዋል።
ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ሙስጠፋ መኪ የዓመቱ ምስጉን ረዳት ዳኛ በመሆን የ105 ሺህ ብር ተሸላሚ ሆነዋል።