በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የእግር ኳስ ክለቦች ሻምፒዮና ውድድር የሆሳዕና ከተማ አሸናፊ ሆነ

ሆሳዕና ፤ ሰኔ 19/2017(ኢዜአ)፡-  የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሁለተኛው  የእግር ኳስ ክለቦች ሻምፒዮና ውድድር በሆሳዕና ከተማ አሸናፊነት ዛሬ  ተጠናቀቀ።

በሆሳዕና  ከተማ  ለተከታታይ 15 ቀናት ሲካሄድ በቆየው በዚሁ ውድድር  የወራቤ ከተማ እና  የእንደጋኝ ሻድጋር ክለቦች ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን አግኝተዋል። 


 

በውድድሩ ማጠናቀቂያ ሥነ-ሥርዓት ላይ  የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ሌሊሾ እንደገለጹት፤ ውድድሩ በክልሉ የአብሮነት እሴት እንዲጎለብት በማድረግ ረገድ  አስተዋጽኦ አበርክቷል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ክልሉን በመወከል የሚጫወቱ  ሶስት  ክለቦችን ለመለየት ማስቻሉንም ጠቁመዋል። 


 

የሆሳዕና ከተማ እግር ኳስ ክለብ አሰልጣኝ ክብረአብ እዮብ በሰጠው አስተያየት፤ የእግር ኳስ ሻምፒዮና ውድድሩ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት እንደሚያግዝ ገልጿል፡፡

በውድድሩ ክለቡ  በአሸናፊነት ማጠናቀቁ በቀጣይ ለተሻለ ውጤት በትጋት እንዲሰራ እንደሚያበረታታው  ተናግሯል።

በውድድሩ አንደኛ ደረጃን በመያዝ ላጠናቀቀው ክለብ ዋንጫ እና የወቅር ሜዳሊያ እንዲሁም ሁለተኛ እና   ሶሰተኛ ደረጃ ላገኙት ክለቦች ደግሞ  የብር እና የነሐስ ሜዳሊያ ተበረክቶላቸዋል።


 

በመርሐ ግብሩ  ማጠናቀቂያ ሥነ-ሥርዓት ላይ   የክልል ፡ የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር አመራሮችና የስፖርት ቤተሰቦች ተገኝተዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም