የአፋር ክልልን የንፁህ መጠጥ ውሃ ሽፋን ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ - ኢዜአ አማርኛ
የአፋር ክልልን የንፁህ መጠጥ ውሃ ሽፋን ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ
አፋር፤ ሰኔ 19/2017 (ኢዜአ) የአፋር ክልልን የንፁህ መጠጥ ውሃ ሽፋን ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት በትኩረት እየተከናወኑ መሆናቸውን የክልሉ ውሃ እና ኢነርጂ ቢሮ ገለፀ።
በአፋር ክልል ቂልበት ረሱ ዞን መጋሌ ወረዳ ገሚሪዳ ቀበሌ በ38 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተመርቆ ለአገልግሎት በቅቷል።
በምረቃ ሰነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የቢሮው ኃላፊ አቶ አህመድ ሻሚ እንደገለፁት የክልሉን የንፁህ መጠጥ ውሃ ሽፋን ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት በትኩረት እየተከናወኑ ናቸው።
በዛሬው ዕለት የተመረቀው የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክትም ለህብረተሰቡ የረጅም ጊዜ ጥያቄ ምላሽ የሰጠና በክልሉ መንግስት እየተገነቡ ካሉ ፕሮጀክቶች አንዱ መሆኑን አንስተዋል።
በፀሐይ ብርሃን ኃይል የሚንቀሳቀሰውና 38 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት ፕሮጀክቱ ከ5 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ገልፀዋል።
በብልፅግና ፓርቲ የዞኑ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሐመድ ሐሰን በበኩላቸው በስፍራው የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተጠናቆ ለአገልግሎት መብቃቱ ማህበረሰቡ ላለፉት ዓመታት በንፁህ መጠጥ ውሃ እጦት ሳቢያ ሲያጋጥመው የነበረውን ችግር እንደሚፈታ ተናግረዋል።
በተለይም እናቶች የመጠጥ ውሃ ለማግኘት ከሚያደርጉት ረጅም ጉዞ እንግልትና በዚህም ምክንያት ሲባክን የነበረውን ጊዜ በመቆጠብ ረገድ እፎይታን የሰጠ ነው ብለዋል።
በምረቃ ስነ ሰርዓቱ ላይም የዞኑና የወረዳ የስራ ኃላፊዎችና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።