የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተጠናቀቀ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 19/2017 (ኢዜአ)፦ በ2017 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጨረሻ ጨዋታ መርሃ ግብር ኢትዮጵያ መድን ስሑል ሽሬን 3 ለ 0 አሸንፏል።
በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ አቡበከር ሳኒ፣ ወገኔ ገዛኸኝ እና ዋንጫ ቱት የማሸነፊያ ግቦቹን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።
ውጤቱን ተከትሎ ሻምፒዮኑ ኢትዮጵያ መድን በ73 ነጥብ አንደኛ ደረጃን ይዞ የውድድር ዓመቱን አጠናቋል። በሊጉም 22ኛ ድሉን አግኝቷል።
ኢትዮጵያ መድን በርካታ ግቦችን ያስቆጠረ፣ አነስተኛ የግብ መጠን ያስተናገደ እና በርካታ ነጥብ የሰበሰበ ቡድን ነው።
ወደ ከፍተኛ ሊግ የወረደው ስሑል ሽሬ በ22 ነጥብ 17ኛ ደረጃን ይዞ ጨርሷል። በውድድር ዓመቱም 18ኛ ሽንፈቱን አስተናግዷል።
ጨዋታውን ተከትሎ መስከረም 10 ቀን 2017 ዓ.ም አሐዱ ብሎ የጀመረው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከዘጠኝ ወራት ቆይታ በኋላ ዛሬ ፍጻሜውን አግኝቷል።
ለመጀመሪያ ጊዜ የሊጉ አሸናፊ የሆነው ኢትዮጵያ መድን ዋንጫውን በመዝጊያ ስነ ስርዓቱ ይረከባል። በቀጣዩ ዓመት ኢትዮጵያን ወክሎ በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ይሳተፋል።