ቀጥታ፡

የጤና መድህን አገልግሎት ተደራሽነትን በማስፋት ሂደት የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለማስተካከል የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

አዳማ፤  ሰኔ 19/2017(ኢዜአ)፡- የጤና መድህን አገልግሎት ተደራሽነትን በማስፋት ሂደት የሚስተዋሉ  ክፍተቶችን ለማስተካከል የሚያስችሉ ተግባራት በቅንጅት እየተከናወኑ መሆኑን የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት ገለፀ።

የጤና መድህን አገልግሎት ተደራሽነትን ለማሳደግ እና የአባላቱ የአገልግሎት እርካታ ላይ የተካሄደው የዳሰሳ ጥናት ግኝቶችና ቀጣይ የመፍትሔ አቅጣጫዎች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በአዳማ ውይይት ተደርጓል።


 

የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ወርቁ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት፤ የህብረተሰቡን የጤና አገልግሎት ተደራሽነት የሚፈታተኑ ማነቆዎችን በዘላቂነት ለመፍታት እየተሰራ ነው።

ዛሬ ይፋ የተደረገው የዳሰሳ ጥናትም በዋናነት ዓላማ አድረጎ የተካሄደው ለጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚዎች ፍትሃዊ የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ነው ብለዋል።

ህብረተሰቡ ፈጣንና ቀልጣፋ የጤና አገልግሎት በፍትሃዊነት እንዲያገኝ ለማስቻል እየተሰራ መሆኑን ገልጸው በቀጣይም የጤና መድህን አገልግሎት ተደራሽነትን በማስፋት ሂደት የሚስተዋሉ  ክፍተቶችን ለማስተካከል የሚያስችሉ ተግባራት  ከባለድርሻ አካላት ጋር  በቅንጅት እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

የአገልግሎቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ  ላምሮት አንዷለም በበኩላቸው፤ የጤና መድህን አገልግሎት በሀገሪቱ 1 ሺህ 90 ወረዳዎች ተደራሽ መደረጉን ገልጸዋል።

በዚህም ከ60 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎች በሀገር አቀፍ ደረጃ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አወስተው፤  እየተገባደደ ባለው በጀት ዓመት ብቻ ከ15 ቢሊዮን ብር በላይ የጤና መድህን ፈንድ ከፌዴራል፣ ክልሎች፣ አባላቱና ባለድርሻ አካላት መሰብሰቡን ተናግረዋል።

ከ4 ሺህ በላይ ከሚሆኑ የጤና ተቋማት ጋር ውል ተገብቶ የጤና አገልግሎት እየተሰጠ እንደሚገኝም ተናግረዋል።


 

በዳሰሳ ጥናቱ መሰረትም ክልሎች ባላቸው የጤና መድህን አባላት ልክ መሰብሰብ የሚገባቸውን ያህል መዋጮ አለመሰብሰብ፣ የአባላት ቁጥር ለመጨመር የሚሰራው ስራ አናሳ መሆን እንዲሁም ብክነትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንደሚታዩ በጥናቱ ተለይቷል ነው ያሉት።

ከዚህም ባለፈ ጠንካራ ክትትልና ቁጥጥር ያለመኖር፣ በተገቢው መልኩ ኦዲት ያለማድረግ ከጥናቱ ግኝቶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል።

የመድረኩ ዓላማም በጥናቱ የተለዩ ክፍተቶችን ለመሙላት የሚያስችል የተቀናጀ ጥረት ለማድረግ መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም በጤና ኢንሹራንስ የፋይናንስ አቅማቸው ራሳቸውን ያልቻሉ ወረዳዎች የችግሮቻቸውን ምክንያት የመለየትና መፍትሔ ለማስቀመጥ ጭምር የተካሄደ ጥናት መሆኑንም አስረድተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም