የስፖርቱን ዘርፍ ህዝባዊ መሰረት እንዲኖረው በማድረግ ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ ይሰራል -ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የስፖርቱን ዘርፍ ህዝባዊ መሰረት እንዲኖረው በማድረግ ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ ይሰራል -ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር

ጅማ፣ ሰኔ 19/2017 (ኢዜአ) የስፖርቱን ዘርፍ ህዝባዊ መሰረት እንዲኖረው በማድረግ ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ እንደሚሰራ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ገለፀ።
በጅማ ከተማ ለአስር ቀናት በ26 የስፖርት ዓይነቶች ሲካሄድ የቆየው የስድስተኛው መላው ኢትዮጵያ የስፖርት ውድድር ዛሬ ተጠናቋል።
በስፖርታዊ ውድድሩም በኦሮሚያ ክልል 224 ሜዳሊያ በማግኘት አንደኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ሲሆን አዲስ አበባ 220 እንዲሁም አማራ ክልል 143 ሜዳልያዎችን በማግኘት ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል።
በውድድሩ መዝጊያ ስነ-ስርዓት ላይም የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታው አቶ መኪዩ መሀመድ እንዳሉት ስፖርቱ ህዝባዊ መሰረት እንዲኖረው በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው።
የስፖርቱን ዘርፍ በማነቃቃት እና ትኩረት እንዲያገኝ ለማድረግ የሚያስችሉ ስራዎች በስፋት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸው በዚህም ህዝቡ በባለቤትነት ተሳትፎ እንዲያደርግ ይሰራል ብለዋል።
ስፖርት እያዝናና መቀራረብንና አብሮነትን የሚያጠናክር በመሆኑ በስፖርቱ የህዝቡን የእርስ በእርስ ትስስር ለማጎልበትም ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ዛሬ የተጠናቀቀው መላው ኢትዮጵያ ጨዋታዎች በዓለም መድረኮች ኢትዮጵያን የሚወክሉ ጠንካራ ስፖርተኞችን ለማፍራትም ትልቅ እድል የፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የኦሮሚያ ክልል የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ሳዳት ነሻ በበኩላቸው፤ በክልሉ የስፖርት ዘርፉ ትልቅ ትኩረት እንደተሰጠው ገልጸዋል።
የክልሉ መንግስት የስፖርት ዘርፉን ለማሳደግ የሚያስችሉ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎችን ጨምሮ ዘርፉን ወደፊት ማምጣት የሚያስችሉ ስራዎች እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
''ስፖርት ወዳጅነትን እና ወንድማማችነትን የምናጎለብትበት ብሎም በዓለም የምንታወቅበት በመሆኑ ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት ይጠናከራል'' ብለዋል።