በፊፋ ክለቦች የዓለም ዋንጫ የምድብ ጨዋታዎች ዛሬ ፍጻሜያቸውን ያገኛሉ 

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 19/2017(ኢዜአ)፦ በፊፋ የክለቦች የዓለም ዋንጫ የምድብ ሰባት እና ስምንት የመጨረሻ ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

በምድብ ሰባት ጁቬንቱስ ከማንችስተር ሲቲ በፍሎሪዳ ካምፒንግ ወርልድ ስታዲየም ከምሽቱ 4 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ። 

ወደ ጥሎ ማለፉ መግባታቸውን ያረጋገጡት ጁቬንቱስ እና ማንችስተር ሲቲ በተመሳሳይ ስድስት ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃን ይዘዋል። 

ጨዋታው የምድቡ መሪ ሆኖ የሚያጠናቅቀውን ቡድን ይወስናል። 

በዚሁ ምድብ በተመሳሳይ ከምሽቱ 4 ሰዓት ላይ ዋይዳድ ካዛብላንካ ከአል አይን በኦዲ ፊልድ ስታዲየም ይጫወታሉ።

በተመሳሳይ ሁለት ሽንፈትን በማስተናገድ ከውድድሩ የተሰናበቱት ዋይዳድ ካዛብላንካ እና አል አይን ያለ ምንም ነጥብ በግብ እዳ ተበላልጠው ሶስተኛ እና አራተኛ ደረጃን ይዘዋል።

የቡድኖቹ ብቸኛ መጽናኛ በውድድሩ ድል አስመዝግቦ ወደ ሀገር ቤት መመለስ ነው። 

በምድብ ስምንት ሳልስበርግ ከሪያል ማድሪድ በሊንከን ፋይናንሻል ፊልድ ስታዲየም፣ አል ሂላል ከፓቹካ በጂኦዲስ ፓርክ ስታዲየም በተመሳሳይ ከሌሊቱ 10 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።

ሪያል ማድሪድ እና ሳልስበርግ በተመሳሳይ አራት ነጥብ በግብ ክፍያ ተባላልጠው አንደኛና ሁለተኛ ደረጃን ይዘዋል።

አሸናፊው ቡድን የምድቡ መሪ ሆኖ ወደ ጥሎ ማለፉ ይገባል። አቻ መውጣት በሂሳባዊ ስሌት ሁለቱንም ቡድኖች ወደ ቀጣዩ ዙር ሊያሸጋግራቸው ይችላል።

አል ሂላል በሁለት ነጥብ ሶስተኛ እና ከውድድሩ የተሰናበተው ፓቹካ ያለ ምንም ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

አል ሂላል ብቸኛ ወደ ጥሎ ማለፍ የሚያልፈው ተጋጣሚውን አሸንፎ ሳልስበርግ እና ሪያል ማድሪድ ከተሸናነፉ ነው።

ፓልሜራስ፣ኢንተር ሚያሚ፣ ፒኤስጂ፣ ቦታፎጎ፣ ቤኔፊካ፣ ባየርሙኒክ፣ ፍላሚንጎ፣ ቼልሲ፣ ቦሩሲያ ዶርትሙንድ፣ ፍሉሚኔንሴ፣ ኢንተር ሚላን፣ ሞንቴሬይ ፣ ጁቬንቱስ እና ማንችስተር ሲቲ ጥሎ ማለፉን የተቀላቀሉ ቡድኖች ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም