የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ይጠናቀቃል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 19/2017 (ኢዜአ)፦ የ2017 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ስሑል ሽሬ እና ሻምፒዮኑ ኢትዮጵያ መድን በሚያደርጉት የ36ኛ ሳምንት ጨዋታ ፍጻሜውን ያገኛል።

የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይካሄዳል። 

ወደ ከፍተኛ ሊግ የወረደው ስሑል ሽሬ በ22 ነጥብ 17ኛ ደረጃን ይዟል። 

በጊዜያዊ ዋና አሰልጣኝ መብራሃቶም ፍስሃ የሚመራው ስሑል ሽሬ በሊጉ ባደረጋቸው 33 ጨዋታዎች ሶስት ጊዜ ሽንፈት ሲያስተናግድ 17 ጊዜ ደግሞ ሽንፈት አስተናግዷል። 13 ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።

ቡድኑ 22 ጎሎችን ሲያስቆጥር 43 ግቦችን አስተናግዷል። ስሑል ሽሬ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ (19) በመቀጠል በሊጉ በርካታ ሽንፈቶችን ያስተናገደ ቡድን ነው። 

ሻምፒዮኑ ኢትዮጵያ መድን በሊጉ እስከ አሁን ባደረጋቸው 33 ጨዋታዎች 21 ጊዜ ሲያሸንፍ 5 ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። 7 ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል። 46 ግቦችን ሲያስቆጥር 15 ግቦችን ተቆጥረውበታል።

በገብረመድህን ኃይሌ የሚሰለጥነው ኢትዮጵያ መድን ከ33ቱ ጨዋታዎች 70 ነጥብ ሰብስቧል። በውድድር ዓመቱ በርካታ ግቦችን ያስቆጠረ፣ አነስተኛ የግብ መጠን ያስተናገደ እና በርካታ ነጥብ የሰበሰበ ቡድንም ነው። 

ኢትዮጵያ መድን ከጨዋታው በኋላ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የግሉ ያደረገውን የሊጉን ዋንጫ ይረከባል። 

በ2017 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመዝጊያ ስነ ስርዓት የኮከቦች ሽልማት ይካሄዳል። 

የዓመቱ ኮከብ ተጫዋች፣ የዓመቱ ኮከብ ተስፈኛ ተጫዋች፣ የዓመቱ ኮከብ ግብ ጠባቂ፣ የዓመቱ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ፣ የዓመቱ ኮከብ አሰልጣኝ፣ የዓመቱ ምስጉን ዋና ዳኛ እና የዓመቱ ምስጉን ረዳት ዳኛ ሽልማት ይበረከትላቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም