ቀጥታ፡

የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት አዋጅ ለሥራ ወደ ውጭ የሚሰማሩ ዜጎችን መብትና ጥቅም በተሻለ መልኩ የሚያስከብር ነው - ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 18/2017(ኢዜአ)፦ የተሻሻለው የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት አዋጅ ለሥራ ወደ ውጭ የሚሰማሩ ዜጎችን መብትና ጥቅም በተሻለ መልኩ የሚያስከብር መሆኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ተናገሩ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ኃብት ልማት፣ ሥራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ የውጭ የሥራ ሥምሪት ረቂቅ አዋጅ ላይ ይፋዊ የሕዝብ ውይይት አካሂዷል።


 

አዋጁን በተመለከተ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል መነሻ ሀሳብ ያቀረቡ ሲሆን በውይይቱ ላይ የተሳተፉ ባለድርሻ አካላትም ያላቸውን ሀሳብና አስተያየት አቅርበዋል።

ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል እንዳሉት፤ አዋጁ ከዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ መርህ ጋር የሚጣጣም ሲሆን ለሥራ ወደ ውጭ ሀገራት የሚሰማሩ ዜጎች ክብርና ጥቅም እንዲጠበቅ ለማድረግ ያለመ ነው።

ወደ ውጭ ሀገራት ለሥራ የሚሰማሩ ዜጎች ተገቢውን ክህሎት እንዲጨብጡ ለማድረግና በመስኩ የሚከናወኑ ሕገ ወጥ ድርጊቶችን በተሻለ መልኩ መቆጣጠር እንደሚያስችል አመልክተዋል።

አዋጁ በሕጋዊ መንገድ ዜጎችን የሚልኩ ኤጀንሲዎች የተሻለ አቅም እንዲፈጥሩ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑን ጠቁመው የሥራ ፈላጊ ምዝገባ፣ ምልመላና ምደባ ሥርዓቱን እንደሚያጠናክር አብራርተዋል።

በውይይቱ ላይ ከተሳተፉት መካከል የውጭ የሥራ ስምሪት አሰሪዎች ፌዴሬሽን ተወካይ መዝገቡ አሰፋ በሰጡት አስተያየት አዋጁ በሥራ ፈላጊዎች ምልመላና ምደባ ላይ ሚኒስቴሩ እንዲሳተፍ የሚፈቅድ መሆኑን አንስተው ይህም ከኤጀንሲዎች ሥራና ኃላፊነት አኳያ እንዴት ይታያል ሲሉ ጠይቀዋል።

የፊውቸር ኢትዮ በውጭ ሀገር የግል ስራና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲ ማህበር ፕሬዝዳንት ሚፍታህ አብዶ በበኩላቸው ኤጀንሲዎች የሚያስቀምጡት የዋስትና ገንዘብ የኤጀንሲዎችን አቅም የሚፈትን እንዳይሆን ሊጤን ይገባል ብለዋል።

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ዳንኤል ተሬሳ በሰጡት ምላሽ አብዛኛዎቹ ኤጀንሲዎች የሚንቀሳቀሱት አዲስ አበባ ላይ በመሆኑ በክልሎች አካባቢ ያለውን ስራ ፈላጊ መልምሎ ተጠቃሚ ማድረግ ላይ ክፍተቶች መኖራቸው በጥናት መለየቱን ገልጸዋል።

ክፍተቱን ለመሙላት የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሰራተኛ ምልመላና ምደባ ስራውን እንዲያከናውን በአዋጁ መደንገጉን አስረድተዋል።

በሰራተኛ ምልመላ ላይ የደላሎች ተሳትፎ መበራከት ሌላው ችግር መሆኑን በጥናት መለየቱን ጠቁመው ይህን ሰንሰለት መቁረጥ አዋጁ ያስፈለገበት ሌላው ምክንያት መሆኑንም ጨምረው አብራርተዋል።

በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሕግ አገልግሎት ሥራ አስፈጻሚ ሲቲና መንግሥቱ በበኩላቸው፥ አንድ ኤጀንሲ ፈቃድ ባወጣ በ6 ወር ውስጥ ሰራተኛ ወደ ውጭ መላክ እንዳለበት በአዋጁ መደንገጉን ጠቁመዋል።

ይህም በህጋዊነት ሽፋን ሊደረጉ የሚችሉ ሕገ-ወጥ ተግባራትን ለመከላከል ያለመ ነው ብለዋል።


 

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ኃብት ልማት፣ ሥራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ(ዶ/ር)፥ ዜጎች ለሥራ ብቁ የሚያደርጋቸውን ክህሎት ሳይወስዱ በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ውጭ እንዳይወጡ በጋራ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

አዋጁ የሥራ ገበያ አማራጭን የሚያሰፋ መሆኑን ገልጸው፥ ኤጀንሲዎች ይህን ዕድል በመጠቀም የተሻለ ሥራ ለማከናወን ይበልጥ መሥራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

አዋጁ ጠቃሚ ግብዓቶች ተካተውበት ጸድቆ ሥራ ላይ እንዲውል ቋሚ ኮሚቴው የድርሻውን እንደሚወጣም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም