ቀጥታ፡

መገናኛ ብዙሃን የኢንዱስትሪ ልማት አጀንዳዎችን ተደራሽ የማድረግ ሚናቸውን አጠናክረው መቀጠል አለባቸው - ሚኒስትር መላኩ አለበል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 18/2017(ኢዜአ)፦ መገናኛ ብዙሃን በድህረ እውነት ዘመን የኢንዱስትሪ ምርትና ምርታማነትን የሚያስተዋውቁና ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ አጀንዳዎችን ተደራሽ የማድረግ ሚናቸውን አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገለጹ።

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በ2017 ዓ.ም የኢትዮጵያ ታምርት ዓመታዊ ኤክስፖና ከርሃብ ነፃ አለም ዓለም አቀፍ ጉባኤ መሳካት አስተዋፅኦ ላበረከቱ የሚዲያ ተቋማት የእውቅና መርሃ ግብር አካሂዷል። 


 

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል እንዳሉት ከርሃብ ነፃ ዓለም ዓለም አቀፍ ጉባኤ ኢትዮጵያ በአምራች ኢንዱስትሪና በግብርና ዘርፍ ያላትን እምቅ አቅም ለዓለም ያሳየችበት እንዲሁም ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን የማስተናገድ የተሟላ አቅም እንዳላት ያስመሰከረችበት ነው። 

የ2017 የኢትዮጵያ ታምርት ዓመታዊ ኤክስፖ ለሶስተኛ ጊዜ የተካሄደና ከዚህ ቀደም ከተካሄዱት በዓይነትና በመጠን ከፍ ያለ የገበያ ትስስር የተፈጠረበት መሆኑንም ተናግረዋል። 

ኤክስፖው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አካል መሆኑን ጠቅሰው ሁለቱም ሁነቶች ዓለም አቀፋዊ ይዘታቸውን ጠብቀው መከናወናቸውን ገልፀዋል። 

በድህረ እውነት ዘመን ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን የሚያረጋግጥ መረጃ ተደራሽ ማድረግ የዘመኑ አርበኝነት መሆኑንም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።


 

የልማት አጀንዳዎችን ማዕከል ያደረጉ፣ የዜጎችን ኑሮ የሚያሻሽሉ ስራዎችን የሚያጠናክሩ ትክክለኛ መረጃዎችን ተደራሽ ማድረግ እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።

የሚዲያ ተቋማት ምርትና ምርታማነትን የሚያስተዋውቁና ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ አጀንዳዎችን ተደራሽ የማድረግ ስራ አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ገልፀዋል። 

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአምራች ኢንዱስትሪውን አቅም በማሳደግ ሀገሪቱ በዘርፉ ያላትን ተወዳዳሪነት ማሳደግ የሚያስችል ነው ብለዋል። 

ለኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖውና ንቅናቄው እንዲሁም ከርሃብ ነፃ ዓለም አቀፍ ጉባዔ መሳካት የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረጉንም ገልጸዋል።

ከሚያዝያ 2014 ዓ.ም ጀምሮ ባለፉት ሦስት ዓመታት የተከናወነው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የግንዛቤ መፍጠሪያ ምዕራፍ በተሟላ መልኩ መሳካቱንም አንስተዋል። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም