በድህረ እውነት ዘመን ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድግ መረጃን ተደራሽ ማድረግ አርበኝነት ነው-የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል - ኢዜአ አማርኛ
በድህረ እውነት ዘመን ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድግ መረጃን ተደራሽ ማድረግ አርበኝነት ነው-የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 18/2017(ኢዜአ) በድህረ እውነት ዘመን ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን የሚያረጋግጥ መረጃ ተደራሽ ማድረግ አርበኝነት መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገለፁ።
የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በ2017 ዓ.ም የኢትዮጵያ ታምርት ዓመታዊ ኤክስፖና ከርሃብ ነፃ አለም ዓለም አቀፍ ጉባኤ መሳካት አስተዋፅኦ ላበረከቱ የሚዲያ ተቋማት የእውቅና መርሃግብር ግብር እያካሄደ ይገኛል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል እንዳሉት ከርሃብ ነፃ ዓለም ዓለም አቀፍ ጉባኤ ኢትዮጵያ በአምራች ኢንዱስትሪና በግብርና ዘርፍ ያላትን እምቅ አቅም ለዓለም ያሳየችበት እንዲሁም ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን የማካሄድ የተሟላ አቅም እንዳላት ያስመሰከረችበት ነው።
የ2017 የኢትዮጵያ ታምርት ዓመታዊ ኤክስፖ ለሶስተኛ ጊዜ የተካሄደና ከዚህ ቀደም ከተካሄዱት በዓይነትና በመጠን ከፍ ያለ የገበያ ትስስር የተፈጠረበት መሆኑንም ተናግረዋል።
ኤክስፖው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አካል መሆኑን ጠቅሰው ንቅናቄው የአምራች ኢንዱስትሪውን አቅም በማሳደግ ሀገሪቱ በዘርፉ ያላትን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ የሚያስችል ነው ብለዋል።
ለኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖና ንቅናቄው እንዲሁም ከርሃብ ነፃ ዓለም ጉባዔ መሳካት የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረጉንም ገልጸዋል።
ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ ባለፉት ሦስት ዓመታት የተከናወነው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የግንዛቤ መፍጠሪያ ምዕራፍ በተሟላ መልኩ መሳካቱንም አንስተዋል።
ለዚህ ስኬት የሚዲያዎች ሚና ከፍተኛ ነው ያሉት ሚኒስትሩ ትክክለኛ መረጃ ለህዝቡ በማድረስ ግንዛቤ እንዲፈጠር አድርገዋል ነው ያሉት።
በድህረ እውነት ዘመን ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን የሚያረጋግጥ መረጃ ተደራሽ ማድረግ የዘመኑ አርበኝነት መሆኑንም አስረድተዋል።