የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ዕርቅና ሠላምን በማስፈን ሂደት ውስጥ የሚጫወቱትን ሚና የበለጠ ማጠናከር አለባቸው - ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ - ኢዜአ አማርኛ
የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ዕርቅና ሠላምን በማስፈን ሂደት ውስጥ የሚጫወቱትን ሚና የበለጠ ማጠናከር አለባቸው - ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 18/2017(ኢዜአ)፦የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ዕርቅና ሠላምን በማስፈን ሂደት ውስጥ የሚጫወቱትን ሚና የበለጠ ማጠናከር እንዳለባቸው የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ገለጹ።
የሰላም ሚኒስቴር "ማህበራዊ ሀብቶቻችን ለህብረ ብሔራዊ አንድነታችን" በሚል መሪ ሀሳብ ሀገር አቀፍ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የጎሳ መሪዎች እና የሰላም ተቋማት አመራሮች የምክክር መድረክ ማካሄድ ጀምሯል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ፥ የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች በሀገራዊ የሰላም ግንባታና አንድነት ላይ ያላቸውን ሚና የሚዳስስ የውይይት መነሻ ጽሁፍ አቅርበዋል።
በጽሁፋቸውም፥ ኢትዮጵያ የውብ ባህልና ታሪክ ባለቤት የሆነች ታላቅ ሀገር መሆኗን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የታሪክ ጉዞም የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች በሀገረ መንግስትና ሰላም ግንባታ የማይተካ ሚና ማበርከታቸውን አንስተዋል።
በተጨማሪም የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ዕርቅና ሠላምን በማስፈን ሂደት ውስጥ የሚጫወቱትን ሚና የበለጠ ማጠናከር እንዳለባቸው ተናግረዋል።
በቀጣይም በሀገራዊ ሰላም ግንባታ ሂደት የመንግስት አጋር በመሆን የተሰጣቸውን ዕውቀትና ጥበብ መጠቀም እንደሚኖርባቸው አስረድተዋል።
የፍትሕ ሥርዓትን በማሳለጥም የሚፈጸሙ ወንጀሎች ትክክለኛ እና ተመጣጣኝ የፍትሕ ምላሽ እንዲያገኙ አይነተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ተናግረዋል።
በዚህም ገለልተኛና ተዓማኒነታቸውን በማስጠበቅ ለመደበኛ የመንግስት አስተዳደር ምክርና ድጋፍ በመስጠት የሞራል ኃላፊነታቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል ብለዋል።
የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ህጋዊነት ከባህላዊ ውርስና ከበሬታ የሚመነጭ መሆኑንም አስረድተዋል።
በአፍሪካ የአመራር ልህቀት አካዳሚ ከዛሬ ሰኔ 18/2017 ዓ.ም ጀምሮ ለሁለት ቀናት በሚቆየው መድረክ የሰላም ሚኒስትር አቶ መሀመድ እድሪስ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ የኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና አባ ገዳዎች ተገኝተዋል።