ኢትዮጵያ በከበሩና በዳበሩ ባህላዊ ሃብቶቿ የሚያጋጥሟትን ችግሮች በጥበብ እየተሻገረች የመጣች ሀገር ናት - ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 18/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በከበሩና በዳበሩ ባህላዊ ሃብቶቿ የሚያጋጥሟትን ችግሮች በጥበብ እየተሻገረች የመጣች ታሪክ ጠገብ ሀገር መሆኗን የሰላም ሚኒስትር አቶ መሀመድ እድሪስ ገለጹ።

የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች በከበሩና በዳበሩ ባህላዊ እሴቶች የኢትዮጵያን ሰላም የማጽናት ኃላፊነት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል። 

የሰላም ሚኒስቴር "ማህበራዊ ሀብቶቻችን ለህብረ ብሔራዊ አንድነታችን" በሚል መሪ ሀሳብ ሀገር አቀፍ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የጎሳ መሪዎች እና የሰላም ተቋማት አመራሮች የምክክር መድረክ ማካሄድ ጀምሯል። 


 

በአፍሪካ የአመራር ልህቀት አካዳሚ ከዛሬ ሰኔ 18/2017 ዓ.ም ጀምሮ ለሁለት ቀናት በሚቆየው መድረክ ላይ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ የኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባ ገዳዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የሰላም ሚኒስትር አቶ መሀመድ እድሪስ በዚሁ ወቅት፥ ኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ታሪክ ባለቤትና የብዝሃ አብሮነት መኖሪያ ትልቅ ሀገር ናት ብለዋል። 

ኢትዮጵያ ልዩነትን በአግባቡ በማስተናገድ የሚያጋጥሟትን ችግሮች በጥበብ እየተሻገረች የመጣች ሀገር መሆኗንም ጨምረው አስገንዝበዋል።  


 

በአህጉሪቷ አፍሪካም ሉዓላዊ አንድነትና ነፃነቷን በማስጠበቅ የዘመናዊ ሀገረ መንግስት ምስረታ ተምሳሌት መሆኗንም ገልጸዋል። 

የከበሩና የዳበሩ ባህላዊ ሃብቶቿም ችግሮች ወደግጭት እንዳያመሩ እና ከተፈጠሩም መፍትሔ በመስጠት የማይተካ ሚና እንዳላቸውን ተናግረዋል።  

በኢትዮጵያ ከ72 በላይ የከበሩና የዳበሩ የሰላም ሃብቶች እንዳሉ ያነሱት ሚኒስትሩ፥ እነዚህም ከራሷ አልፎ ሌሎችን ጭምር ማስማማት የሚችሉ ናቸው ብለዋል። 


 

የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ከአያት ቅድመ አያቶች የተወረሱ ባህላዊ ጥበቦች ባሉባት ኢትዮጵያ በትናንሽ ችግሮች ህይወትና ንብረትን የሚያጠፉ ግጭቶች ሊፈጠሩ እንደማይገባ አንስተዋል። 

የግጭት አካሄድ ያረጀና ያፈጀ፥ ማንንም የማይጠቅም ነው ያሉት አቶ መሀመድ፥ መንግስት የፈጠረውን የሰላም አማራጭ ጥሪ ተከትሎም በኦሮሚያና አማራ ክልሎች የሚንቀሳቀሱ አካላት ከተሳሳተ አካሄዳቸው እየተመለሱ ይገኛሉ ብለዋል። 

በቀጣይም የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች የኢትዮጵያን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ በሚደረገው ጥረት ገንቢ ሚናቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል። 

የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር)፥ የሰላም ጉዳይ የሁላችንም ትብብር የሚፈልግ መሰረታዊ ጉዳይ ነው ብለዋል። 


 

የመድረኩ ዓላማም የሀገርን ሰላም አጽንቶ ለማስጠበቅ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች የሰላም ግንባታ ስራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ለማስቻል መሆኑን ገልጸዋል። 


 

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ለምክክር መድረኩ የሀገር ሽማግሌዎች በሀገራዊ የሰላም ግንባታና አንድነት ላይ ያላቸውን ሚና የሚዳስስ የውይይት መነሻ ጽሁፍ አቅርበው ውይይት መካሄድ ጀምሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም