የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ውጤታማነትን ለማረጋገጥ የባለድርሻ አካላትን ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር ይገባል-ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ውጤታማነትን ለማረጋገጥ የባለድርሻ አካላትን ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር ይገባል-ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ሰኔ 17/2017 (ኢዜአ)፦የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ውጤታማነት ለማረጋገጥ የባለድርሻ አካላትን ቅንጅታዊ አሰራርን ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባ የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ገለጹ።
ትምህርት ሚኒስቴር የብሄራዊ የቅድመ ልጅነት ዘመን እድገት እና ትምህርት ፖሊሲ ማዕቀፍ ትግበራ እና ቀጣይ አቅጣጫ አስመልክቶ ያዘጋጀው ውይይት ተካሄዷል።
የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) የቅድመ ልጅነት ዘመን እድገትና ትምህርት ፖሊሲ ኢትዮጵያን ወደሚፈገለው የለውጥ መዳረሻ ለመውሰድ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል።
መንግስት ህጻናት የማይናወጥ፣ ፍትሃዊ እና አካታች የሆነ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት እንዲያገኙ አበክሮ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ቅድመ ልጅነት ላይ መዋዕለ ንዋይን ማፍሰስ የእድሜ ልክ ትርፍን የሚያስገኝ ነው ያሉት ሚኒስትሯ፥ ይህም ጤናማ ማህበረሰብ ለመገንባት፣ ለሀገራዊ ኢኮኖሚ እና ለሀገር ልማት ወሳኝ ሚና አለው ብለዋል።
ስር የሰደደ ድህነትን ለማጥፋት፣ሁሉን አቀፍ እድገት ለማስመዝገብ በመልካም ስብዕና የተገነባ ትውልድን ለመፍጠር ህጻናት ላይ መስራት ጉልህ አበርክቶ እንዳለው አመልክተዋል።
የበጀት ስርዓቱን ማጠናከር፣በሰው ኃይል ላይ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ እና ወላጅና ማህበረሰቡን በማሳተፍ ውጤታማነትን ማላቅ ይገባልም ነው ያሉት።
የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሸቴ ትምህርት ለብልፅግና መረጋገጥ እና ዜጎች የልማት ተቋዳሽ እንዲሆኑ ጉልህ ሚና እንዳለው አመልክተዋል።
ለሀገር ሁለንተናዊ ብልፅግና ወሳኝ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በለውጡ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ተደራሽነት አንዱ ነው ብለዋል።
በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ በሺዎች የሚቆጠሩ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መገንባታቸውን ጠቁመው፤ በዚህም የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ተደራሽነት በየዓመቱ ከስድስት በመቶ በላይ እያደገ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
የተገኙ ውጤቶች እና ያሉ ተግዳሮቶችን በመፍታት የቅድመ ልጅነት ዘመን እድገት እና ትምህርትን የበለጠ ለማጠናከር ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንዲያደርጉ ሚኒስትር ዴኤታዋ ጥሪ አቅርበዋል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ በበኩላቸው፥ የቀዳማይ ልጅነት ዘመን በጤናው ዘርፍ ያሉ ዘላቂ ልማት ግቦች እና የጤና እቅዶችን ለማሳካት ቁልፍ መሆኑን ገልጸዋል።
ቀዳማይ ልጅነትን ከጤና ዘርፉ ጋር በማሰናሰን የሀገር ብልፅግና እና ልማትን እውን ለማድረግ የጋራ ስራ ያስፈልጋል ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው።
በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ማሪኮ ካጊሾማ ኢትዮጵያ ተራማጅ የሆኑ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ፖሊሲ እና አሰራር በመተግበር እያከናወነች ያለውን ስራ አድንቀዋል።
ዩኒሴፍ ለቀጣይ የኢትዮጵያ እድገት እና ልማት መሰረት ለሆነው የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) በመዲናዋ የቀዳማይ ልጅነት ዘመን ትምህርት ላይ ለሌሎች ተሞክሮ የሚሆን መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይ ተደራሽነቱን ለማስፋት በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ሀቢባ መሐመድ በክልሉ መንግስት ከፍተኛ አመራሮች የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋት ባከናወነው ስራ በርካታ ውጤቶች መገኘታቸውን ጠቅሰው ስኬቶችን የማላቅ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት፣እድገት እና ስነ ልቦና ተመራማሪ ፕሮፌሰር በላይ ተፈራ፥ መንግስት ጥራት ያለው የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ተደራሽነት ለማሳደግ ብቁ የሰለጠነ ኃይል ማፍራት፣ የስልጠና ስርዓት አማራጮችን እንደ ተጨባጭ ሁኔታዎች መጠቀም እና የስርዓተ ትምህርቱ ላይ ያሉ አሰራሮችን መፈተሽ እንደሚገባው አመልክተዋል።
የአፍሪካ የቀዳማይ ልጅነት ልማት ማዕከል የትምህርት እና ቀዳማይ ልጅነት ማስፋፊያ ፕሮግራም ስራ አስኪያጅ ታቦር ገብረመድህን (ዶ/ር) በሀገር አቀፍ በደረጃ በቅድመ ልጅነት ላይ የተሰሩ ስራዎች አበረታች ውጤቶች መመዝገቡን በጥናት አረጋግጠናል ብለዋል።