በአፍሪካ ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጂ በመጠቀምና በላቀ አመራር ምርጥ ተብሎ መሸለም ለተሻለ ስራ ያነሳሳል -ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል

አዲስ አበባ፤ሰኔ 17/2017(ኢዜአ)፦በአፍሪካ ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጂ በመጠቀም በተደራጀ መንገድ በብቃት የሚመራ ተቋም ተብሎ መሸለም ለተሻለ ስራ መነሳሳትን የሚፈጥር መሆኑን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ፡፡

ኢትዮጵያ ከሰኔ 14 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ለሶስት ተከታታይ ቀናት በአፍሪካ ሕብረት የመሰብሰቢያ አዳራሽ በትይዩ ሲካሄድ የነበረውን 10ኛው የአፍሪካ የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር እንዲሁም የመንግሥታቱ ድርጅት የአፍሪካ ቀጣናዊ ፎረምን በስኬት አጠናቃለች።

በፎረሙ በተዘጋጀው ኤግዚቢሽን የመንግሥትን አገልግሎት ይዘው ከቀረቡ ተቋማት መካከል የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አንዱ ነው።

ኮሚሽኑ ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጂ በመጠቀም እንዲሁም ቀልጣፋና የላቀ አገልግሎት በመስጠት አንደኛ ደረጃን በመያዝ ከአፍሪካ ሕብረት የዋንጫ ተሸላሚ ሆኗል።

የፌደራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር መኩሪያ ሃይሌ (ዶ/ር) የዋንጫ ሽልማቱን ለኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል አስረክበዋል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የፖሊስ የአገልግሎት አሰጣጡን በማዘመንና በማቀላጠፍ የዜጎችን ደህንነት በአስተማማኝ ሁኔታ እየጠበቀ ነው።

በዚህም የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ላይ በተካሄደው ዓለም አቀፍ ውድድር ምርጥ የፖሊስ መተግበሪያ ሽልማት ማግኘቱን አስታውሰዋል።

በአፍሪካ ሕብረት በተካሄደው የአፍሪካ የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ስብሰባ እና በተመድ የአፍሪካ ቀጣና ፎረም ላይ ፖሊስ ያለውን ልምድና አቅም ለአፍሪካውያን አካፍሏል ብለዋል።

በዚህም የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በቴክኖሎጂ በመታገዝ በብቃት በመምራትና በላቀ አገልግሎት አንደኛ በመውጣት የዋንጫ ተሸላሚ መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በስራው ያገኘው ሽልማትና እውቅና በቀጣይ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት መነሳሳት የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።

በአፍሪካ ሞዴል የፖሊስ አገልግሎት የመስጠት ራዕይ ሰንቀን እየሰራን ነው ያሉት ኮሚሽነር ጀነራሉ፥ በቀጣይ አዳዲስ አሰራሮችን በመተግበር ለተሻለ አገልግሎት እንተጋለን ብለዋል።

በቅርቡ በሰው ሰራሽ አስተውሎት የታገዘ በአፍሪካ የመጀመሪያው በዓለም አራተኛውን ስማርት ፖሊስ ጣቢያ ወደ ስራ ለማስገባት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ መተግበሪያ ጋር የተቀናጀ በየትኛውም ዓለም የሚመጡ ግለሰቦችን በቀላሉ የጸጥታ ድጋፍ ማድረግ የሚያስችል ቀላል አሰራር መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ስማርት የፖሊስ ጣቢያው ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካውያን ወንድሞቻችን በሞዴልነት የምናሸጋግረው ነው ብለዋል፡፡

የፌደራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሌ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የአፍሪካ ሕብረት አባል ሀገራት በመንግሥት አገልግሎት አቅማቸው ተወዳድረው ኢትዮጵያ የተሻለ ዝግጅት እንዳላት ተለይቶ ሁነቱን እንድታዘጋጅ መደረጉን ገልጸዋል።

የሽልማት ውድድሩ በአፍሪካ ሕብረት የተደረገ መሆኑን ገልጸው፣ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በቴክኖሎጂ በመታገዝ በተደራጀና በብቃት የሚመራ ተቋም ተብሎ የውድድሩን ትልቁን የወርቅ ሽልማት አሸንፏል ብለዋል።

ሽልማቱ ፖሊስ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ ያሸነፈችበት መሆኑን ገልጸው፣ በተደራጀ መንገድ የላቀ አገልግሎት መስጠት የሚያኮራ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም