በክልሉ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

ሐረር፤ሰኔ 17/2017 (ኢዜአ)፦በሐረሪ ክልል የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ጨምሮ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ገለፀ።
በክልሉ የሚገኙ የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋማትም የትራፊክ አደጋን በመቀነስ ረገድ በኃላፊነት እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።
የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ፈቲህ ቶውፊቅ እንዳሉት፥ በክልሉ የአሽከርካሪ ብቃት ማነስና ቸልተኝነት፣ የተሽከርካሪ ቴክኒክ ችግሮችና የመንገዶች ጥበት ለትራፊክ አደጋ መከሰት በምክንያትነት ይጠቀሳሉ።
ችግሮቹን ለመቀነስም ቢሮው በዚህ ዓመት ብቻ ከ4 ሺ በላይ ለሚሆኑ አሽከርካሪዎች የመንገድ ደህንነት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን አከናውኗል።
በትምህርት ቤቶችም የመንገድ ደህንነት ክህሎት እና የትራፊክ ክበባትን በማቋቋም አደጋ የመቀነስ ተግባራት እየተከናወኑ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
የአሽከርካሪ ብቃትን የማረጋገጥ ስራዎችንም ከማሰልጠኛ ተቋማት ጋር በመሆን እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመው፥ ከተሽከርካሪ የቴክኒክ ችግሮች ጋር በተያያዘም የአውቶሜሽን ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልፀዋል።
በተለይ በከተማው የተከናወነው የኮሪደር ልማት ስራ ለእግረኛና ለብስክሌት ምቹ ሁኔታን በመፍጠሩ ከመሰረተ ልማት ጋር በተያያዘ ይከሰቱ የነበሩ የትራፊክ አደጋዎችን ሙሉ ለሙሉ ማስቀረቱን አመልክተዋል።
በትራፊክ አደጋ ሳቢያ ለአካል ጉዳት የተዳረገው ወጣት ዳግም ሰለሞን እንደገለፀው፥ በደረሰበት አደጋ ለስነ ልቦና ጉዳት ከመዳረጉም ባለፈ ከስራው መስተጓጎሉን ተናግሯል።
የትራፊክ አደጋ መንስዔ የአሽከርካሪዎች ቸልተኝነትና ብቃት ማነስ መሆኑን ገልፆ፥ አደጋው የሰው ህይወትና አካልን ለጉዳት ከማጋለጡም በላይ በንብረት ላይ የሚደርሰውም አደጋ ከባድ መሆኑን አስረድቷል።
የሐረር ኢንተርናሽናል አሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋም ስራ አስኪያጅ አቶ ኤርሚያስ ጀርመን በበኩላቸው፥ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የአሽከርካሪዎች ባህሪ ላይ መስራት የማሰልጠኛ ተቋማት ቀዳሚ ተግባር መሆኑን ገልፀዋል።
የአሽከርካሪው የቴክኒክ ብቃት በሰውና በንብረት ላይ የሚደርስ አደጋን ለመቀነስ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ከግንዛቤ በማስገባት ተቋማቸው ለተግባራዊነቱ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ተቋማቸው በቴክኖሎጂ የበለጸገ ስልጠና እየሰጠ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የአዜብ አሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋም ባለቤትና ስራ አስኪያጅ አቶ መሀዲ አዲስ ናቸው።
ለትራፊክ አደጋ መከሰት የብቃት ማረጋገጫ የሌለውና የእድሜ ገደብን ያላማከለ ሃሰተኛ የመንጃ ፈቃድ ተጠቃሽ መሆናቸውን ተናግረው፥ በዚህ ረገድ በክልሉ እያጋጠመ ያለውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ በኃላፊነት እንደሚሰሩም ጠቁመዋል።
የመንገድ ደህንነትና መድህን ፈንድ አገልግሎት በክልሉ በመንገድ ደህንነት ዙሪያ የተሰሩ ስራዎች፣ በአሽከርካሪ ማሰልጠኛና የተሸከርካሪ ምርመራ ተቋማት የሚሰጡት የስልጠናና የቴክኒክ ምርመራ አሰራር፣ በኮሪደር ልማቱ የመንገድ ደህንነት አስተዋፅኦና ሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ምልከታ ማከናወኑ ይታወሳል።