ትምባሆ በጤና ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ ለመከላከል የህጎች ተፈፃሚነትን ማረጋገጥ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ትምባሆ በጤና ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ ለመከላከል የህጎች ተፈፃሚነትን ማረጋገጥ ይገባል
አዲስ አበባ፤ሰኔ 17/2017(ኢዜአ)፦ትምባሆ በጤና ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ ለመከላከል የህጎችን ተፈፃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የኢትዮጵያ ምግብና መድህኒት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሔራን ገርባ ገለፁ፡፡
በሰዎች ላይ ከፍተኛ የጤና መታወክ በማስከተል ለማህበራዊ ብሎም ለኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተጋላጭ እያደረጉ ካሉ መንስኤዎች መካከል ትንባሆ ተጠቃሽ እንደሆነ ይገለፃል።
በተለይ ወጣቶች የትንባሆ ተጠቃሚ መሆናቸው አምራችና ጤናማ የሰው ሀይል እንዳይኖር ከማድረጉ ባለፈ የሱስ ተጠቂ ሆነው ህይወታቸው እንዲሰናከል ያደርጋቸዋል፡፡
በዚህም ባለስልጣኑ ሀገሪቱን ከትንባሆ ስጋት ለማላቀቅና በዘርፉ ላይ ያለውን ቁጥጥር ለማጠናከር ከብሄራዊ የትምባሆ ቁጥጥር አስተባባሪ ኮሚቴ ተቋማት ጋር ዛሬ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል፡፡
የኢትዮጵያ ምግብና መድህኒት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሔራን ገርባ፣ ትንባሆ በህብረተሰብ ጤና ላይ የሚፈጥረውን ችግር ለመፍታት ጠንካራ የሕግ ማዕቀፎችን በማውጣት ተግባራዊ መደረጉን ገልጸዋል።
ባለስልጣኑም እ.ኤ.አ በ2016 የዘርፉ ባለድርሻ የሆኑና 30 የሚጠጉ ተቋማትን በማካተት ብሄራዊ የትንባሆ ቁጥጥር አስተባባሪ ኮሚቴ በማቋቋም ትንባሆ የሚያሳድረውን ተጽእኖ ለመፍታት የሚያስችሉ ተግባራት በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ከእነዚህ መካከል ተቋማት ከትንባሆ ጭስ ነጻ እንዲሆኑ ማድረግ ፣ ግንዛቤ ማስጨበጥ እና በጉዳዩ ላይ የሚወጡ ህጎችን ተፈጻሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።
የመግባቢያ ስምምነት ሰነዱ ስራዎች ወጥነት እንዲኖራቸው ለማስቻል እንዲሁም በተናበበ እና በተቀናጀ መንገድ ለማስኬድ የሚረዳ ነው ተብሏል፡፡
ስምምነቱ ለብሄራዊ አስተባባሪ ኮሚቴው የትንባሆ ቁጥጥር ስትራቴጂ እቅድን በጋራ ለመገምገም አቅም የሚፈጥር መሆኑ ተገልጿል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ተቋማትን ከትንባሆ ጭስ ነጻ ለማድረግ ብሎም ለሰራተኞች አስፈላጊውን ስልጠና በመስጠት ችግሩን ለመከላከል አቅም ይፈጥራል ብለዋል።