የሕዝቡን ትስስር እና የሰላም ግንባታ ለማጠናከር ያለመ የባህልና ቋንቋ ንቅናቄ ይካሄዳል - ሚኒስቴሩ - ኢዜአ አማርኛ
የሕዝቡን ትስስር እና የሰላም ግንባታ ለማጠናከር ያለመ የባህልና ቋንቋ ንቅናቄ ይካሄዳል - ሚኒስቴሩ

አዳማ፤ ሰኔ 17/2017(ኢዜአ)፡- የሕዝቡን ትስስር እና የሰላም ግንባታ ለማጠናከር ያለመ የባህልና ቋንቋ ንቅናቄ ከሀምሌ 1 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ለሶስት ወራት ሊካሄድ መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ ''የባህል ብልፅግና ለሀገረ መንግስት ግንባታ'' በሚል መሪ ሀሳብ ሀገር አቀፍ የባህል እና ቋንቋ ንቅናቄ ሰነድና የማስፈፀሚያ ስልት ላይ ያተኮረ ውይይት ከባለድርሻ አካላት ጋር በአዳማ አካሂዷል።
በመድረኩ የተገኙት የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ነፊሳ አልመሀዲ፤ እንዳስታወቁት ከሀምሌ 1 ቀን 2017 እስከ መስከረም 30/2018 የሚቆይ ሀገር አቀፍ የባህልና ቋንቋ ንቅናቄ ይካሄዳል።
የንቅናቄው ዓላማ ብዝሀ ባህልና ቋንቋ ለማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ልማት ያለውን ሚና ለማሳደግ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተለይ ባህልና ቋንቋ ለሀገረ መንግስት ግንባታና ለህዝቦች ትስስር እንዲሁም ለሰላምና ዕድገት ፈር ቀዳጅ በመሆኑ በአግባቡ መጠቀም ይገባል ብለዋል።
በዚህ ረገድ በንቅናቄው ከሚከናወኑ አበይት ተግባራት መካከል ከቀበሌ ጀምሮ በባህል ዘርፍ ያሉ እሴቶች ጎልተው እንዲወጡ ማስቻል አንዱ መሆኑን አመልክተዋል።
በተጨማሪም የባህል ፌስቲቫሎችን በሁሉም ክልሎች በማካሄድ የባህል መገልገያ መሳሪያዎችና ጌጣ ጌጦች እንዲሁም የሽምግልናና የእርቅ ስርዓቶችን ለትውልድ ግንባታ ለማዋል ጥረት እንደሚደረግም ገልፀዋል።
በሀገር አቀፍና በክልል ደረጃ የሚከበሩ በዓላትን በአግባቡ አጥንቶ በሁሉም መስክ ጥቅም ላይ በማዋል በኩል ያሉ ውስንነቶችን ለማሻሻል ጭምር ንቅናቄው ያግዛል ብለዋል።
በንቅናቄው ማህበረሰቡን የሚያስተሳስሩ፤ ወንድማማችነትንና እህትማማችነትን የሚያጠናክሩ ውይይቶችና ኤግዚቢሽኖች በየደረጃው እንደሚካሄድም አስረድተዋል።
እነዚህን እቅዶች ማስፈፀም የሚያስችል ሰነድ መዘጋጀቱንም ሚኒስትር ዴኤታዋ አስታውቀዋል።
በሚኒስቴሩ የባህልና ቋንቋ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ ተስፋነሽ ተሎሬ(ዶ/ር) በበኩላቸው ዜጎች ባህላዊ እሴቶቻቸውን እንዲጠብቁና እንዲያሳድጉ ሚኒስቴሩ እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
በተለይ ባህልና ቋንቋ ሀገራዊ መግባባት እንዲጠናከር ያላቸውን ሚና በመገንዘብ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራበት እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
በሚቀጥሉት ሶስት ወራት ሊካሄድ የታሰበው ንቅናቄ ባህላዊ ሀብቶችን ለማዳበር፤ ህብረ ብሄራዊ አንድነትን ለማጠናከር፤ ባህልን ለወል ትርክት ግንባታ ለማዋል እንዲሁም ወጣቶች ባህላቸውን በሚገባ እንዲያውቁና እንዲጠብቁ ገንቢ ሚና እንዳለውም አስረድተዋል።
በመድረኩ የሚኒስቴሩ ተጠሪ ተቋማት ኃላፊዎች፤ ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ ባለድርሻ አካላትና የሴት አደረጃጀቶች ተገኝተዋል።