ቀጥታ፡

ዩኒሴፍ በኢትዮጵያ ለቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ውጤታማነት የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚቀጥል ገለጸ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 17/2017(ኢዜአ)፦ የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት(ዩኒሴፍ) ኢትዮጵያ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋትና አጠቃላይ ውጤታማነትን ለማረጋገጥ እያከናወነች ያለውን ስራ መደገፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ።

ትምህርት ሚኒስቴር የብሄራዊ የቅድመ ልጅነት ዘመን እድገትና ትምህርት ፖሊሲ ማዕቀፍ ትግበራ እንዲሁም ቀጣይ አቅጣጫን አስመልክቶ ያዘጋጀው ውይይት እየተካሄደ ነው።

በምክክሩ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር)፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሸቴ፣ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ፣ በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት(ዩኔሴፍ) ምክትል ተወካይ ማሪኮ ካጎሺማ፣ የፌደራልና የክልሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የልማት አጋር ድርጅቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተወካዮች ተገኝተዋል።


 

በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ ምክትል ተወካይ ማሪኮ ካጎሺማ ለአንድ ሀገር እድገት የቀዳማይ ልጅነት ዘመን ላይ ጊዜ ሰጥቶ መስራት ቀጣይ ትውልድን ለመገንባት ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።

በዚህ ረገድ መንግስት በቅድመ አንደኛ ደረጃ ስርዓት ላይ እየተገበራቸው ያሉ ፖሊሲዎችና አሰራሮች የሚደነቁ ናቸው ብለዋል።

የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ተደራሽነት ላይ ያሉ ለውጦች አበረታች መሆናቸውን ተናግረዋል።

ዩኒሴፍ ለብሄራዊ የቅድመ ልጅነት ዘመን እድገትና ትምህርት ፖሊሲ ማዕቀፍ ቀረጻ እና ትግበራ ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰዋል።

በቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት በተለይም ተፈናቃዮችን፣ ልዩ ፍላጎት ያላቸው ዜጎችንና ተጋላጭ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝም አመልክተዋል።

በተጨማሪም ድርጅቱ በዘላቂ የትምህርት ስርዓት ማጠናከሪያ ማዕቀፍ አማካኝነት በኢትዮጵያ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርትን እየደገፈ መሆኑን አንስተዋል።

ዩኒሴፍ ለኢትዮጵያ እድገትና ልማት መሰረት ለሆነው የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት በቀዳማይ ልጅነት ደረጃ ትምህርት ላይ እየተገበራቸው ባሉ ኢንሼቲቮች ያለው የፖለቲካ ቁርጠኝነትና የፋይናንስ ድጋፍ በዘላቂነት እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ተደራሽነት ማስፋት የጋራ ትብብርን እንደሚጠይቅ ጠቅሰው ለዚህም ዘርፈ-ብዙ የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም