የተፈናቃዮችን ጉዳይ በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ ለመመለስ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የተፈናቃዮችን ጉዳይ በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ ለመመለስ እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 17/2017(ኢዜአ)፦የተፈናቃዮችን ጉዳይ የህዝቡን የጋራ ዘላቂ ተጠቃሚነትና አብሮነት በሚያረጋግጥ መልኩ በሰላማዊና በህጋዊ መንገድ እንዲፈታ የጋራ አቋም በመያዝ እየተሰራ መሆኑን የመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ገለጹ።
ተፈናቃዮችን በኃይል ለመመለስ የሚሞክር ኃይል ቢኖርም እኛ በሰላማዊና በህጋዊ መንገድ እንዲመለሱ ጽኑ አቋም እንዳለን ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ጨምሮ ሁሉም አካል ሊያውቀው ይገባል ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ-መስተዳደር አቶ አረጋ ከበደ ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ-መስተዳደር አቶ አረጋ ከበደ እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ በሁመራ ከተማ በወልቃይት ጠገዴ የማንነት ጥያቄና በተፈናቃዮች ጉዳይ ላይ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ተወያይተዋል።
የፌዴራል መንግሥት የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነትን ተግባራዊ በማድረግ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ እንዲሁም የማንነትና የአስተዳደር ጥያቄ ያለባቸው አካባቢዎች በሰላማዊ መንገድ እልባት እንዲያገኙ በትኩረት እየሰራ ይገኛል።
የአማራ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አረጋ ከበደ የማንነትና የራስ አስተዳደር ጥያቄ ያላቸው አካባቢዎችን በተመለከተ በፌዴራል መንግሥት አማካይነት ላለፉት ዓመታት ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር በርካታ ውይይቶች ሲደረጉ መቆየታቸውን አውስተዋል።
አንዱ በጥልቀት ውይይት ሲደረግበት የቆየው የወልቃይት ጠገዴ የማንነትና የአስተዳደር ወሰን ጉዳይ እና የተፈናቃዮች መመለስን በተመለከተ መሆኑንም ገልጸዋል።
ተፈናቃዮችን በኃይል ለመመለስ የሚሞክር ኃይል ቢኖርም እኛ በሰላማዊና በህጋዊ መንገድ እንዲመለሱ ጽኑ አቋም እንዳለን ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ጨምሮ ሁሉም አካል ሊያውቀው ይገባል ብለዋል።
ሰላማዊ አማራጭ ለህዝቦች አብሮነትና ዘላቂ ጥቅም ወሳኙ መንገድ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው የህዝቡን የጋራ እጣ ፈንታና ተጠቃሚነት ማዕከል ያደረገ ስራ መስራት የግድ ነው ብለዋል።
ከቀድሞ የህወሃት አመራሮች በኩል የወልቃይት ጠገዴ ማንነት ጥያቄን ከመሸፋፈን ባለፈ ተፈናቃዮችን በኃይል መመለስ አለብን በሚል የጦርነት ነጋሪት የሚጎስሙ መኖራቸውን አንስተዋል።
የትግራይ ህዝብ ዋነኛ አጀንዳ ሰላም ነው ያሉት አቶ ጌታቸው ህዝቡን ከቀድሞ ህወኃት አመራር ለይቶ ማየት እንደሚገባም ጠቁመዋል።
የወልቃይት ጠገዴ የማንነትና የአስተዳደር ወሰን ጥያቄ ህጋዊ መሆኑን ገልጸው ጥያቄው በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ሁላችንም ልንሰራ ይገባል ብለዋል።
የትግራይ ወጣት ዳግም የጦርነት ሰለባ መሆን እንደማይፈልግ በማንሳት ከዚህ ቀደም በስህተት በተገባበት ጦርነት የደረሰው ኪሳራ እንዳስተማረውም ገልጸዋል።
በመሆኑም ከዚህ ቀደም የነበሩ በደሎችን በማከም ለተሻለ መጻኢ ጊዜ በጋራ መስራትና መወያየት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ተፈናቃዮችም በሰላማዊ መንገድ እንዲመለሱ መስራት ከሁሉም አካል እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል።
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አስተዳዳሪ አሸተ ደምለው እና ምክትል አስተዳዳሪ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ በበኩላቸው፥ የማንነት ጥያቄውና የተፈናቃዮች መመለስ ጉዳይ በህጋዊና ሰላማዊ መንገድ ብቻ እንዲፈታ ነው የምንፈልገው ብለዋል።
ለዚህም ሰላማዊ ውይይትን አጠናክሮ መቀጠልና ዘላቂ መፍትሔ ላይ መድረስ እንደሚገባ በመጠቆም።