ቀጥታ፡

በልጆች ላይ የሚፈሰው መዋዕለ ንዋይ የወደፊቷን ኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ የሚወስንና ለብልፅግና መረጋገጥ መሰረት የሚጥል ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 17/2017(ኢዜአ)፦ በልጆች ላይ  የምናፈሰው መዋዕለ ንዋይ እና የምናከናውነው ስራ የወደፊቷን ኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ የሚወስንና ለብልፅግና መሰረት የሚጥል ነው ሲሉ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር  ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ገለጹ።

ትምህርት ሚኒስቴር የብሄራዊ የቅድመ ልጅነት ዘመን እድገት እና ትምህርት ፖሊሲ ማዕቀፍ ትግበራ እና ቀጣይ አቅጣጫ አስመልክቶ ያዘጋጀው ውይይት እየተካሄደ ነው።


 

በምክክሩ ላይ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ፣ የትምህርት ሚኒስቴር የአጠቃላይ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አየለች እሸቴ፣ የመንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) የቅድመ ልጅነት ዘመን እድገትና ትምህርት ፖሊሲ ኢትዮጵያን ወደሚፈገለው የለውጥ መዳረሻ ለመውሰድ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል።

መንግስት ህጻናት የማይናወጥ፣ ፍትሃዊ እና አካታች የሆነ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት እንዲያገኙ አበክሮ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ቅድመ ልጅነት ላይ መዋዕለ ንዋይን ማፍሰስ የእድሜ ልክ ትርፍን የሚያስገኝ ነው ያሉት ሚኒስትሯ ይህም ጤናማ ማህረሰብ  ለመገንባት፣ ለሀገራዊ ኢኮኖሚ እና ለሀገር ልማት ወሳኝ ሚና አለው ብለዋል።

ስር የሰደደ ድህነትን ለማጥፋት፣ ሁሉን አቀፍ እድገት ለማስመዝገብ በመልካም ስብዕና የተገነባ ትውልድን ለመፍጠር ህጻናት ላይ መስራት ጉልህ አበርክቶ እንዳለው አመልክተዋል።

መንግስት በሰጠው ትኩረት ከ500 በላይ ህጻናት ማቆያና የቀን የመንከባከቢያ ስፍራዎች በተለያዩ የሀገሪቷ ክፍሎች መገንባታቸውን ጠቁመዋል።

በገጠር አካባቢ የሚኖሩ ተጋላጭ የማህረሰብ ክፍሎች ፍትሃዊ የትምህርት ተደራሽነት፣ የመምህራን የተጠናከረ ስልጠና አለማግኘት፣ የግብአት አቅርቦት፣ ፋይናንስ እና የትምህርት መመዘኛ በሚገባ አለመተግበር የዘርፉ ተግዳሮቶች ናቸው ብለዋል።

የበጀት ስርዓቱን ማጠናከር፣ በሰው ኃይል ላይ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ እና ወላጅና ማህበረሰቡን በማሳተፍ ውጤታማነትን ማላቅ ይገባልም ነው ያሉት።


 

የትምህርት ሚኒስቴር የአጠቃላይ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አየለች እሸቴ ትምህርት  ለብልፅግና መረጋገጥ እና ዜጎች የልማት ተቋዳሽ እንዲሆኑ ጉልህ ሚና እንዳለው አመልክተዋል።

በተለይም በቅድመ ልጅነት የሚከናወኑ ተግባራት ለሀገር ሁለንተናዊ ብልፅግና ወሳኝ መሆናቸውን ጠቅሰው በለውጡ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ተደራሽነት አንዱ ነው ብለዋል።

የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት በትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ እና በቅርቡ በፀደቀው የአጠቃላይ ትምህርት አዋጅ እንዲካተት መድረጉን ለማሳያነት ጠቅሰዋል።

የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ተደራሽነት ማስፋት እና ህጻናትን በለጋ እድሜያቸው ማስተማር ያጋጠመውን የትምህርት ስብራት ለመጠገንና ለመቀየር ወሳኝ እንደሆነም ነው ሚኒስትር ዴኤታዋ የገለጹት።

በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ በሺዎች የሚቆጠሩ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መገንባታቸውን ጠቁመው በዚህም የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ተደራሽነት በየዓመቱ ከስድስት በመቶ በላይ እያደገ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

2012 ዓ.ም የነበረው የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ተደራሽነት 42 በመቶ እንደነበረ አስታውሰው ምጣኔው በ2016 ዓ.ም ወደ 57 በመቶ ከፍ ማለቱን ጠቁመዋል።

የተገኙ ውጤቶች እና ያሉ ተግዳሮቶችን በመፍታት የቅድመ ልጅነት ዘመን እድገት እና ትምህርትን የበለጠ ለማጠናከር ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንዲያደርጉ ሚኒስትር ዴኤታዋ ጥሪ አቅርበዋል።

በምክክሩ ላይ ሀገር አቀፍ የቀዳማይ ልጅነት እድገትና የትምህርት ፖሊሲ አቅጣጫ የተመለከተ ሰነድ ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት ነው።

የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት እድሜያቸው ከአራት እስከ ስድስት ዓመት የሆናቸው ህጻናት ጨዋታን መሰረት ባደረገ የማስተማር ስነ-ዘዴ ዕውቀት የሚያገኙበት የትምህርት አይነት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም