ወንጪ-ደንዲ ኢኮ ቱሪዝም መንደር እና ሎጅ ተፈጥሮ፣ ታሪክ፣ ቅርስ እና ባህል በአንድ ተሳስሮ የሚገኝበት ድንቅ አካባቢ ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 17/2017(ኢዜአ)፦ ወንጪ-ደንዲ ኢኮ ቱሪዝም መንደር እና ሎጅ ተፈጥሮ፣ ታሪክ፣ ቅርስ እና ባህል በአንድ ተሳስሮ የሚገኝበት ድንቅ አካባቢ ነው ሲሉ የሕዝብ እና የግል መገናኛ ብዙሃን አመራሮችና ባለሞያዎች ገለጹ።

ከመላው ኢትዮጵያ የተውጣጡ የህዝብ እና የግል መገናኛ ብዙሃን ባለሞያዎች ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ጋር በተለያዩ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸዉ ይታወቃል፡፡

ከውይይቱ በኋላ ባለሙያዎቹ የወንጪ-ደንዲ ኢኮ ቱሪዝምን ጎብኝተዋል።


 

በዚሁ ወቅት የኢዜአ ምክትል ሥራ አስፈፃሚ ፍፁምእሸት ሽመልስ እንዳሉት ወንጪ-ደንዲ ኢኮ ቱሪዝም መንደር እና ሎጅ ተፈጥሮ፣ ታሪክ፣ ቅርስ እና ባህል በአንድ ተሳስሮ የሚገኝበት ድንቅ አካባቢ ነው።

ሀገር ያላትን ፀጋ በሚገባ አይቶ የማልማት፣ የመጠበቅና የማቆየት ሥራን በግልፅ ያሳየ አካባቢ እንደሆነም ተናግረዋል።

ወንጪ-ደንዲ ኢኮ ቱሪዝም መንደር እና ሎጅ-ከማህበረሰቡ ጋር ከልብ የተሳሰረ አስደናቂ የቱሪስት መዳረሻ መሆኑን መመልከታቸውን ገልጸዋል።

የመገናኛ ብዙሃን ይህን ሥራ በማስተዋወቅ በኩል የበኩላቸውን እየተወጡ ቢሆንም የበለጠ መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

የኦሮሚያ ብሮድካስት ኔትወርክ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አንዋር ጀማል በበኩላቸው ወንጪ-ደንዲ ኢኮ ቱሪዝም መንደር እና ሎጅ በጥበበኞች የተሰራ ድንቅ የተፈጥሮ መዳረሻ መሆኑን ገልጸዋል።

መሰል የቱሪስት መዳረሻዎችን የመገናኛ ብዙሃንና ባለሙያዎች በማስተዋወቅ በኩል በትኩረት መስራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የህግ አገልግሎት መምሪያ ሥራ አስፈፃሚ አበረ አዳሙ የወንጪ አስደማሚ ተፈጥሮ ዘመናዊነት ታክሎበት ከተሰራ በኋላ ድንቅ አካባቢ ሆኖ መቀጠሉን ጠቅሰዋል።

መንግስት በተፈጥሮ የታደሉ አካባቢዎችን በመለየት እያለማ ያለው ሥራ አበረታች እና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ነው ብለዋል።

እንደ አንድ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያ የተሰሩ ሥራዎችን በማስተዋወቅ ረገድ የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ ነው ያረጋገጡት።

ኪንግ ኦፍ አባይ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ዛይድ ዘይዳን መዳረሻው ኢትዮጵያ ያላትን የቱሪዝም ሀብት ገልጦ ያሳየ ድንቅ ቦታ ነው ብለዋል።

እነዚህ ሥራዎች የሀገራችንን ቱሪዝም በማሳደግ በኩል ጉልህ ሚና እንደሚጫወቱ ተናግረው፤ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች መዳረሻዎችን ለማስተዋወቅ በስፋት መስራት አለብን ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም