ቀጥታ፡

ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርዓት የፍትህ ተደራሽነትን እያሳደገ ይገኛል - ሚኒስቴሩ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 17/2017(ኢዜአ)፦ ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርዓት የፍትህ ተደራሽነትን እያሳደገ እንደሚገኝ የፍትህ ሚኒስትር ሀና አርአያስላሴ ተናገሩ።

በኢትዮጵያ የሕግ ስርዓት ውስጥ ባህላዊ የግጭት መፍቻ ዘዴን ለማካተት መወሰድ በሚገባቸው ወሳኝ እርምጃዎች ላይ ያተኮረ ሀገራዊ ምክክር እየተካሄደ ይገኛል።

በምክክር መድረኩ የፍትህ ሚኒስትር ሀና አርአያስላሴ፣ የፍትህ ሚኒስትር ዲኤታዎች፣ የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቶችና የመንግስት የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል።

የፍትህ ሚኒስትር ሀና አርአያስላሴ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት በኢትዮጵያ ላለፉት አመታት ግጭቶች በባህላዊ የፍትህ ስርዓት ሲፈቱ ቆይቷል።

ህብረተሰቡ ለበርካታ ዘመናት ሲጠቀምባቸው የቆዩ ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርዓቶች የህግ ዕውቅና እንዲያገኙ፣  እንዲበረታቱ እና እንዲስፉፉ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

መንግስት በፍትሕ ትራንስፎርሜሽን እቅዱ የማህበረሰብ ፍትህ ተቋማት እንዲስፋፉ በማድረግ እውቅና እየሰጠ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡

ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርዓት የፍትህ ተደራሽነትን እያሳደገ መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሯ በዚህም በማህበረሰቡ መካከል የሚከሰቱ ግጭቶች እየተፈቱበት መሆኑን ጨምረው ጠቅሰዋል።

በቀጣይ የባህላዊ ግጭት አፈታት ስርዓትን ማጠናከር የሚያስችሉ ስራዎች በትኩረት ይሰራሉ ብለዋል።

የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ ኤርሚያስ የማነብርሀን(ዶ/ር) በበኩላቸው ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርዓቶች በቀላሉ ተደራሽ፣ ወጪና ጊዜ ቆጣቢ በመሆናቸው ውጤታማ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ተናግረዋል።

ምክክሩ የማህበረሰብ ፍትህ ስርዓትን ለማስፋፋት የተጀመረውን ጥረት ለማጠናከር ወሳኝ መሆኑንም አንስተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም