ቀጥታ፡

ረቂቅ አዋጁ ቅንጅታዊ አሰራሮችን የሚያጠናክርና የዜጎችን ደህንነት፣ ብቃትና ተወዳዳሪነት ማጎልበት የሚያስችል ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 16/2017(ኢዜአ)፦ የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ረቂቅ አዋጅ ቅንጅታዊ አሰራሮችን የሚያጠናክርና የዜጎችን ደህንነት፣ ብቃትና ተወዳዳሪነት ማጎልበት የሚያስችል መሆኑ ተመላከተ።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት፣ ስራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በውጭ ሀገር ስራ ስምሪት ረቂቅ አዋጅ ላይ ከስራና ክህሎት ሚኒስቴር ሀላፊዎች ጋር ተወያይቷል።


 

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አዋጁን ማስፈጸም የሚያስችል የሰው ሀይል የማደራጀትና ሌሎች የዝግጅት ስራዎችን ማከናወንን ጨምሮ የአዋጁ ማስፈጸሚያ ደንብና መመሪያዎችን የማዘጋጀት ስራ ከወዲሁ በትኩረት ሊሰራ ይገባል።

አዋጁ በተለያዩ ሙያዎች ሰልጥነው ስራ የሚፈልጉ ዜጎችን ማካተቱ እንዲሁም፣ ኤጀንሲዎች በማህበር ተደራጅተው እንዲሰሩ የሚያደርግ መሆኑ መልካም ነው ብለዋል።

በረቂቅ አዋጁ ላይ የጤና ምርመራ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ምርጫ፣ የኮሚሽን ድርድር በኤጀንሲዎችና ፌዴሬሽን ብቻ መገደቡና የባህረኞችና የሹፌሮች የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት ላይ ያተኮሩ ጥያቄዎች ከቋሚ ኮሚቴውና የህግ ጥናት ዳይሬክቶሬት ቀርበዋል።

የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በሰጡት ምላሽ ረቂቅ አዋጁ ቅንጅታዊ አሰራሮችን የሚያጠናክርና የዜጎችን ደህንነት፣ ብቃትና ተወዳዳሪነት ማጎልበት የሚያስችል ነው ብለዋል።

ህገወጥነትን ከመከላከል አንጻርም ቀደም ሲል በነበረው አዋጅ ላይ የታዩ ክፍተቶችን መፍታትና ጠንካራ እርምጃዎች መውሰድ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

የዜጎችን ደህንነት ከማስጠበቅ፣ ሀገሪቱ ከውጭ ምንዛሬ ማግኘት ያለባትን ገቢ፣ በዘርፉ የዳበረ ልምድ ያላቸው ሀገራትን ተሞክሮ መሰረት በማድረግ የኮሚሽን ድርድር በኤጀንሲዎች ብቻ እንዳይደረግ መደረጉን ጠቅሰዋል።

በውጭ ሀገራት የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ አመራር አባል እና ቤተሰቦች የኤጀንሲ ፍቃድ እንዳያገኙ ክልከላ የተደረገው የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅና የጥቅም ግጭትን ለመከላከል መሆኑንም አንስተዋል።

የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተሻለ በሬቻ(ዶ/ር) ወደ ውጭ ሀገራት ለስራ ስምሪት የሚሄዱ ዜጎች ብቁና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ በመዳረሻ ሀገራት ከሚቀያየሩ ሁኔታዎች አንጻር የክለሳ ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን አንስተዋል።

የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ዳንኤል ተሬሳ በበኩላቸው፤ የዜጎችን ደህነነት ለማስጠበቅና ህገወጥነትን ለመከላከል በማሰብ በረቂቅ አዋጁ ጠንካራ ህጎች መካተታቸውን ገልጸዋል።

በምክር ቤቱ በተደጋጋሚ ሲነሳ የነበረው የኤጀንሲዎች መብዛትንም በጋራ ሆነው እንዲሰሩና ለአስተዳዳር ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር በማህበር እንዲደራጁ የሚያስችል መሆኑንም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም