በአፍሪካ ዘላቂ የውሃ አቅርቦትና ደህንነትን ለማረጋገጥ በጋራ መስራት ያስፈልጋል - አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
በአፍሪካ ዘላቂ የውሃ አቅርቦትና ደህንነትን ለማረጋገጥ በጋራ መስራት ያስፈልጋል - አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 16/2017(ኢዜአ)፦ በአፍሪካ ዘላቂ የውሃ አቅርቦት እንዲኖርና የውሃ ደህንነት እንዲረጋገጥ በጋራ መስራት ያስፈልጋል ሲሉ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ(ዶ/ር) ገለፁ።
የኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ከጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ (ጃይካ) ጋር በመተባበር ያዘጋጀው በውሃ ልማት ላይ ያተኮረ ዓለም አቀፍ ስልጠና ማስጀመሪያ መርሃግብር ተካሂዷል።
ከዛሬ ጀምሮ ለ25 ቀናት በሚሰጠው ስልጠና ከኢትዮጵያ እና ሱዳን የተውጣጡ የዘርፉ ባለሙያዎች ይሳተፉበታል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ(ዶ/ር)፥ በአፍሪካ የህዝብ ቁጥር መጨመርና ለብክነት የሚዳርግ አጠቃቀም የውሃ ተደራሽነት ችግር እንዲከሰት አድርጓል ብለዋል።
የተቋማት አቅም ማነስ በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ውጤታማና ዘላቂ የውሃ አገልግሎት እንዳይኖር እያደረገ ነው ያሉት አምባሳደር አስፋው በአፍሪካ የውሃ ደህንነትን ለማረጋገጥ በጋራ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በ2030 ንፁህና ደህንነቱ የተጠበቀ በቂ ውሃን ለሁሉም ዜጋ ተደራሽ ለማድረግ በርካታ ተግባራት እያከናወነች እንደምትገኝ ሚኒስትር ደኤታው ገልጸዋል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ምክትል ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር መለስ አለም(ዶ/ር) በበኩላቸው ኢትዮጵያና ሱዳን ለዘመናት የዘለቀ ጠንካራ ወዳጅነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን ተናግረዋል።
የውሃ ልማት ላይ ያተኮረ ዓለም አቀፍ ስልጠናው የሁለቱን ሀገራት የውሃ ዘርፍ ባለሙያዎች ትብብርና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት የሚያጠናክር መሆኑንም ጨምረው አስታውቀዋል።
ጃይካ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር እየሰራባቸው ካሉት ዘርፎች መካከል የውሃ አቅርቦት መሆኑን የገለፁት ደግሞ በኢትዮጵያ የጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ(ጃይካ) ተወካይ ኬንሱኬ ኦሺማ ናቸው።
ጃይካ ኢትዮጵያና ሱዳንን ጨምሮ በአፍሪካ በውሃ ዘርፍ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ታመነ ሀይሉ(ዶ/ር) ኢንስቲትዩቱ እስካሁን ከአሥራ ስምንት ሀገራት ለተውጣጡ ባለሙያዎች ስልጠና መስጠቱንና በቀጣይም ይህን ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ያብራሩት።