ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የምትሳተፍበት የአፍሪካ- አሜሪካ የቢዝነስ ጉባኤ በሉዋንዳ ተጀመረ

 

አዲስ አበባ፤ሰኔ 16/2017 (ኢዜአ)፦የአፍሪካ-አሜሪካ የቢዝነስ ጉባኤ የተለያዩ የአፍሪካ አገራት መሪዎችና የአሜሪካ መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በአንጎላ ሉዋንዳ በይፋ ተጀምሯል።

በኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ የተመራው የኢትዮጵያ ልዑክ ቡድን በጉባኤው ለመሳተፍ ትናንት እኩለ ቀን ላይ ሉዋንዳ መድረሱን ኢዜአ ከሥፍራው ዘግቧል።

ልዑክ ቡድኑ አንጎላ ሲደርስ በአገሪቱ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል።

የዘንድሮውን የአፍሪካና የአሜሪካ የቢዝነስ ጉባኤ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር አሜሪካ አፍሪካን በተመለከተ የምትከተለው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ድጋፍን መሰረት ካደረገው ወደ ንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ለመቀየር የመወሰኑትን ውሳኔ ተከትሎ የሚካሄድ መሆኑ ልዩ ያደርገዋል።


 

ጉባኤው በአንጎላ መካሄዱ በተለይም የአገሪቱ ነጻነቷን ከተቀዳጀች 50 ዓመቷን በምታከብርበት ወቅት ላይ መሆኑና የአንጎላ ፕሬዝዳንት ጆኣኦ ሎሬንሶ የአፍሪካ ኅብረት የወቅቱ ሊቀ-መንበር በሆኑበት ወቅት መሆኑም ሌላው ልዩ የሚያደርገው ነው።

በዚህ ጉባኤ የተለያዩ የአፍሪካ አገራት መሪዎች፣ሚኒስትሮች፣ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የአሜሪካ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣የሁለቱም ወገን የቢዝነስ መሪዎችን ጨምሮ 1 ሺህ 500 ተሳታፊዎች ይታደማሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ጉባኤው በአፍሪካና በአሜሪካ መካከል ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር በሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችና እድሎች ዙሪያ በመምከር ቀጣይ አቅጣጫዎችን እንደሚያስቀምጥ ታምኖበታል።

በጉባኤው ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ንግግር የሚያደርጉ ሲሆን ከጉባኤው ጎን ለጎንም የተለያዩ የሁለትዮሽ ውይይቶችን እንደሚያደርጉ ኢዜአ ከስፍራው ዘግቧል።

በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ልዑክ ቡድን አባላትም በጉባኤው በፓናል ውይይትና በሌሎች ስብሰባዎች ላይ ተሳትፎ ያደርጋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም