ሪያል ማድሪድ በፊፋ ክለቦች ዓለም ዋንጫ የመጀመሪያ ድሉን አሳክቷል - ኢዜአ አማርኛ
ሪያል ማድሪድ በፊፋ ክለቦች ዓለም ዋንጫ የመጀመሪያ ድሉን አሳክቷል

አዲስ አበባ ፤ ሰኔ 15/2017(ኢዜአ)፦ በፊፋ የክለቦች ዓለም ዋንጫ በምድብ ስምንት ሪያል ማድሪድ ፓቹካን 3 ለ 1 አሸንፏል።
ማምሻውን በቻሮሌት ባንክ ኦፍ አሜሪካ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ጁድ ቤሊንግሃም በ35ኛው፣ አርዳ ጉለር በ43ኛው እና ፌዴሪኮ ቫልቬርዴ በ70ኛው ደቂቃ ላይ ግቦቹን አሳርፈዋል።
ኤሊያስ ሞንቲዬል በ80ኛው ደቂቃ ለፓቹካ ብቸኛዋን ጎል አስቆጥሯል።
የሪያል ማድሪድ ተከላካይ ራኡል አሴንሲዮ በሰባተኛው ደቂቃ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል።
ከ80 ደቂቃ ላይ በ10 ተጫዋች የተጫወተው ሪያል ማድሪድ ለማሸነፍ አልተቸገረም።
በጨዋታው ጅማሮ የተሻለ እንቅስቃሴ ያደረጀው ፓቹካ ያገኘውን የተጫዋች ብልጫ አልተጠቀመበትም።
ውጤቱን ተከትሎ በፊፋ የዓለም ክለቦች ዋንጫ የመጀመሪያ ድሉን ያሳካው ሪያል ማድሪድ በአራት ነጥብ ምድብ ስምንትን መምራት ጀምሯል።
ዣቪ አሎንሶ በሪያል ማድሪድ አሰልጣኝነት የመጀመሪያ ድሉን አግኝቷል።
በውድድሩ ሁለተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ፓቹካ ከውድድሩ ተሰናብቷል።
በምድብ ስምንት ሳልስበርግ ከአል ሂላል ከሌሊቱ 7 ሰዓት ላይ በዋሺንግተን ዲሲ ኦዲ ፊልድ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ሳልስበርግ በሶስት ነጥብ ሁለተኛ፣ አል ሂላል በአንድ ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።