የኮሪደር ልማት አስቀድሞ መከላከል የጤና ፖሊሲን በተግባር ለማዋል ታስቦ እየተሰራ ያለ ልማት ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የኮሪደር ልማት አስቀድሞ መከላከል የጤና ፖሊሲን በተግባር ለማዋል ታስቦ እየተሰራ ያለ ልማት ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 15/2017(ኢዜአ)፦ የኮሪደር ልማት በአፍ ሲነገር የቆየውን አስቀድሞ መከላከል የጤና ፖሊሲን በተግባር ለማዋል ታስቦ እየተሰራ ያለ ልማት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከመላው ኢትዮጵያ ከተውጣጡ የጤና ባለሞያዎች ጋር ተወያይተዋል።
በውይይቱም የጤና ባለሙያዎች የኮሪደር ልማቱን ከአስቀድሞ የመከላከል የጤና ፖሊሲ ነጥለው ማየት እንደሌለባቸው አንስተዋል።
የኮሪደር ልማት በአፍ ሲነገር የቆየውን አስቀድሞ መከላከል የጤና ፖሊሲን በተግባር ለማዋል ታስቦ እየተሰራ የሚገኝ ልማት መሆኑን አስገንዝበዋል።
ከለውጡ በፊት ለ30 ዓመታት ሲተገበር የቆየው የጤና ዘርፍ ፖሊሲ መከላከል ላይ ያተኮረ መሆኑን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከለውጡ በኋላ ግን የታመመ ማከም ላይም መስራት ስለሚገባ የፖሊሲ ክለሳ ተደርጓል ነው ያሉት።
በመሆኑም ከለውጡ በኋላ በጤናው ዘርፍ እየተተገበረ የሚገኘው የጤና ፖሊሲ መከላከል እና ማከምን አጣምሮ የያዘ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ ፖሊሲ በመከላከል ብቻ የማይገቱ በሽታዎችን ማከም የሚያስችል አቅም መገንባት አስፈላጊ በመሆኑ እንደሆነ ጠቅሰው ለዚህም የኮቪድ ወረርሽኝን ለአብነት ጠቅሰዋል።
የጤና ዘርፍ ባለሙያዎች የኮሪደር ልማቱን ከመከላከል የጤና ዘርፍ ፖሊሲ ነጥለው መመልከት እንደሌለባቸውም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስገነዘቡት።
በኮሪደር ልማቱ እየተከናወኑ የሚገኙት የእግረኛ መንገዶች፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችና የወንዝ ዳርቻ ልማቶች የበሽታ መንስኤ የነበሩ አካባቢዎችን ማልማት ከመከላከል የጤና ፖሊሲ ጋር በቀጥታ የሚገናኝ መሆኑን አብራርተዋል።
ሁሉም የሚሰራው ስራ ከጤና ጋር በቀጥታ የሚገናኝ መሆኑን አንስተው ንጹህ ለመሆን፣ ጽዱ አካባቢ ለመፍጠርና ሰዎች አካላዊ ንቃት እንዲኖራቸው ለማድረግ የሚሰሩ ስራዎች በሙሉ ከጤና ብሎም ከመከላከል የጤና ፖሊሲ ጋር በቀጥታ የሚገናኙ ናቸው ብለዋል።