ቁጭትን በትምህርት ያሳኩ ታታሪው ግለሰብ - ኢዜአ አማርኛ
ቁጭትን በትምህርት ያሳኩ ታታሪው ግለሰብ

አቶ ዘይኔ መሀመድ ይባላሉ። የስልጤ ዞን ወራቤ ከተማ ነዋሪ ናቸው።
አቶ ዘይኔ ያላቸውን የትምህርት ደረጃ ለማሻሻል ዘወትር ሲፈልጉና ያሉበት ደረጃ አልዋጥ ብሏቸው፤ ሳያምኑበት ለዘመናት ሲቆጩበት ኖረዋል።
ታዲያ ቁጭታቸውን በትምህርት ለመወጣትም ከሚሰሩበት ስልጤ ዞን ስልጢ ወረዳ በመምጣት የወራቤ ዩኒቨርሲቲ ባወጣው ክፍት የስራ ቦታ ላይ ለመቀጠር አመለከቱ፡፡
ከዚያም አስፈላጊውን ነገር በማሟላት በዩኒቨርሲቲው ክፍት የስራ መደብ ማለትም በጉልበት ሰራተኝነት በመቀጠር በእንጨት ፈላጭነት ስራ እንደጀመሩ ይናገራሉ፡፡
ቁጭታቸውን በልባቸው ይዘው ዓላማቸውን ለማሳካት ያለምንም መታከት ስራቸውን ሲከውኑ ቆይተው በ1999 ዓ.ም በተፈጥሮ ሀብት አጠባበቅ ትምህርት መስክ በዲፕሎማ መርሐ ግብር ተመረቁ፡፡
ዩኒቨርሲቲውም በተማሩበት የትምህርት መስክ የውበት ጥበቃ ባለሙያ ሆነው እንዲያገለግሉ በመመደብ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ዕድልን አመቻቸላቸው፡፡
በተመደቡበት የግቢ ውበት ጥበቃ የስራ ዘርፍ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣታቸውንና ለስራቸው ያላቸውን ተነሳሽነት የተመለከተው የዩኒቨርስቲው አስተዳደርም የትምህርት ደረጃቸውን እንዲያሻሽሉ እድል ሰጣቸው፡፡
ያገኙትን እድል በመጠቀም በተፈጥሮ ሀብት አጠባበቅ ትምህርት መስክ የመጀመሪያ ዲግሪ ተከታትለው በማጠናቀቅ ለምረቃ በቅተዋል
የሰው ልጅ ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለመድረስ ስራን ባለመናቅ ጊዜን በአግባቡ በመጠቀም ከሰራ ህልሙን ለማሳካት የሚያግደው አንዳችም ነገር እንደሌለም አቶ ዘይኔ ያነሳሉ፡፡
ሁሉም የተሰጠውን የስራ ኃላፊነት በሚገባው ልክና በተገቢው መንገድ መወጣት ከቻለ የስራው ውጤት እራሱ ይናገርለታል ይላሉ፡፡
ምቹ ሁኔታን ብቻ በመሻት ስኬት እንደሌለ የሚያነሱት አቶ ዘይኔ ዝቅ ብሎ መስራት ወዳለሙት የስኬት ጎራ ለመድረስ እንደ መስፈንጠሪያ ሊጠቅም እንደሚችልም ይመክራሉ፡፡
ዛሬ በበርካታ ተግዳሮት ውስጥ ሆነው ያገኙት የመጀመሪያ ዲግሪ ነገን ወደ ተሻለ የትምህርት ደረጃ ተስፈንጥረው ለማደግ መነሻ ይሆንልኛል ብለውም ያምናሉ።
በተለይ ወጣቶች ስራን ሳያማርጡ በመስራት ወደ ተሻለ ምዕራፍ መድረስን ከኔ የህይወት ተሞክሮ መማር ይኖርባቸዋል ሲሉም በአፅንኦት ይመክራሉ።
በዩኒቨርሲቲው የግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ ተወካይ ዲን አቶ አላሙዲን ቁፋ፣ አቶ ዘይኔ በግቢው ከሚሰሩት ስራ በተጨማሪ በትምህርት ክፍሉም ታታሪና ተሳትፏቸው የላቀ ተማሪ እንደሆኑም መስክረዋል፡፡
ይህም በትምህርት ክፍሉ የተሰጠውን የመውጫ ፈተና በአጥጋቢ ውጤት ለማለፍ እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።
በመደበኛነት ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙ ተማሪዎች የመውጫ ፈተና ለማለፍ በርካታ ተግዳሮቶች እንደሚገጥማቸው ገልጸው ተመራቂው አቶ ዘይኔ በዩኒቨርሲቲው የተሰጠውን የመውጫ ፈተና በበቂ ውጤት ማለፍ መቻላቸውም ለሌሎች ተሞክሮ የሚሆን ነው ብለዋል፡፡