ቀጥታ፡

ተመራቂዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ያዳበሩትን የመቻቻልና የወንድማማችነት እሴቶች በማጎልበት ሀገርን ማሻገር ይጠበቅባቸዋል

መቱ፤ ሰኔ 15/2017(ኢዜአ)፦ ተመራቂዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ያዳበሩትን የመቻቻል፣ የአብሮ መስራት፣ የወንድማማችነትንና መሰል እሴቶችን በማጎልበት ሀገርን ወደፊት ማሻገር እንደሚጠበቅባቸው የመቱ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አለሙ ዲሳሳ(ዶ/ር) አስገነዘቡ።

መቱ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን 2ሺህ 157 ተማሪዎች በዛሬው ዕለት አስመርቋል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት አለሙ ዲሳሳ(ዶ/ር) በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት በዩኒቨርሲቲ የሚሰጠውን የንድፈ ሐሳብ ትምህርት አጠናቆ መመረቅ ለተመራቂዎች ትልቁ ምዕራፍ መሆኑን ገልጸዋል።

ተመራቂዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ያዳበሯቸውን የመቻቻል፣ የአብሮ መስራት፣ የወንድማማችነትና መሰል እሴቶችን በማጎልበት ሀገርን ወደፊት የማሻገር ኃላፊነት እንደተጣለባቸው ተናግረዋል።

ምሩቃን በተማሩት የትምህርትን መስክ ሀገርንና ሕዝባቸውን በቁርጠኝነት፣ በታማኝነትና በሀገር ወዳድነት ስሜትና አመለካከት ለማገልገል ቁርጠኛ መሆን እንዳለባቸውም አመልክተዋል።

ተመራቂዎች እንደሀገር በተለያዩ መስኮች የተቀረጹ የልማት ኢኒሼቲቮችን እውን በማድረግ ሀገራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በተመረቁበት መስክ በቁርጠኝነትና በታማኝነት የማገልገል ትልቅ ኃላፊነት እንደተጣለባቸው የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር እና የዩኒቨርሲቲው ስራ አመራር ቦርድ አባል ጌታቸው ቶሌራ(ዶ/ር) ናቸው።

በአግሮ-ኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ተመራቂ እና የዋንጫ ተሸላሚው ዮብሰን አንጋሳ በበኩሉ ባገኘሁት እውቀትና ሙያ ሀገሬን ለመለወጥ የበኩሌን ለማበርከት ዝግጁ ነኝ ብሏል።

በተለይ በግብርናው ዘርፍ እየታዩ የሚገኙ አስደናቂ ለውጦችን በማስቀጠል በኩል የዜግነት ኃላፊነቱን በተቻለው አቅም ሁሉ አንደሚወጣ ገልጿል።

ፈይሳ ዲንቂና ዮናስ ሱራፌል የተባሉ ተመራቂዎችም በተመሳሳይ የተጀመሩ ሁለንተናዊ ሀገራዊ የልማት ስራዎችን በማስቀጠል ሀገራዊ ብልጽግና እንዲረጋገጥ የበኩላቸውን አሻራ ለማኖር እንደሚጥሩ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም