ለሀገር የሰሩ እና መልካም ዓላማ የነበራቸው አመራሮች ሲያልፉ ራዕያቸው ፍሬ እንዲያፈራ ማድረግ ያስፈልጋል - ሚኒስትር መላኩ አለበል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 15/2017(ኢዜአ)፦ ለሀገር ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ የሰሩ እና መልካም ዓላማ የነበራቸው አመራሮች ሲያልፉ ሃሳባቸው ህያው እንዲሆንና ራዕያቸው መሬት ወርዶ ፍሬ እንዲያፈራ ማስታወስ ይገባል ሲሉ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገለጹ።

በህዝብ የተጣለባቸውን ሀላፊነት በመወጣት ላይ እንዳሉ በግፍ የተሰዉትን የአማራ ክልል የቀድሞ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮንን እና ሌሎች ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች 6ኛ አመት የሰማዕትነት መታሰቢያ መርሀ ግብር “ያለፈውን ማክበር፣ የወደፊቱን መከተል” በሚል መሪ ሀሳብ ተከናውኗል።


 

በመርሃ ግብሩ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የፌደራል ዋና ኦዲተር መሰረት ዳምጤ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ እና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሀላፊ ጃንጥራር አባይ እና ሌሎች የፌዴራልና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግስት የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል በወቅቱ እንዳሉት፤ ለሀገር ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ የሰሩ እና መልካም ዓላማ የነበራቸው አመራሮች ሲያልፉ ራዕያቸው መሬት ወርዶ ፍሬ እንዲያፈራ ማስታወስ ያስፈልጋል።

በየአመቱ የሰማዕታቱ መታሰቢያ ሲደረግም እነዚህ ዓላማዎቻቸውን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በዶክተር አምባቸው ስም የተቋቋመው ፋውንዴሽን ህልማቸው በነበሩት ጤና፣ ትምህርት፣ የሀገር ልማት እና ሰላም ዙርያ ትኩረት አድርጎ እየሰራ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል።

ትምህርት የሀገርን እድገት ፍትሃዊነትና የኢትዮጵያን መፃኢ እጣ ፈንታ የሚያረጋግጥ በመሆኑ ህልማቸውን እውን ለማድረግ የሁሉም ርብርብ ያስፈልጋል ብለዋል።

የዶክተር አምባቸው መኮንን ፋውንዴሽን ስራ አስኪያጅ መአዛ አምባቸው በበኩላቸው፤ ፋውንዴሽኑ በጥናትና ምርምር የታገዘ ስራ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ዶክተር አምባቸው ለሀገርና ለህዝብ የሚጠቅም የጠራ ራዕይ እንደነበራቸው በተለያዩ ተቋማት ያከናወኗቸው ተግባራት ህያው ምስክር መሆናቸውንም አንስተዋል።

በስማቸው ፋውንዴሽን በማቋቋም በህይወት ቢኖሩ ሊፈጽሟቸው ይችሉ የነበሩትን ህልሞች ለመተግበር እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

ችግኝ በመትከል እንዲታሰቡ የተደረገውም ፋውንዴሽኑ ካሉት የትኩረት መስኮች ዋነኛው አረንጓዴ ልማትን በመደገፍ አሻራችንን ለማሳረፍ ነው ብለዋል።


 

የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ደረጄ እንግዳ በበኩላቸው፤ ዶክተር አምባቸው በህይወት በነበሩበት ወቅት የዩኒቨርሲቲው የቦርድ ሰብሳቢ በመሆን በርካታ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን ጠቅሰዋል።

በዚህም የእርሳቸው መታሰቢያ እንዲሆን በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ጊቢ ሀገር በቀልና የፍራፍሬ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር መከናወኑን ገልፀዋል።

የዶክተር አምባቸው መኮንን እና ሌሎች ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች 6ኛ አመት የሰማዕትነት መታሰቢያን ምክንያት በማድረግ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ተከናውኗል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም