ተመራቂዎች የቀሰሙትን እውቀት ለአገር እድገት ማዋል አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
ተመራቂዎች የቀሰሙትን እውቀት ለአገር እድገት ማዋል አለባቸው
ደብረ ብርሃን፤ ሰኔ 15/ 2017 (ኢዜአ)፡- ተመራቂዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የቀሰሙትን እውቀትና ክህሎት ለሀገር እድገት ማዋል እንዳለባቸው የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አስማረ መለሰ (ዶ/ር) አስገነዘቡ።
የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ለ18ኛ ጊዜ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን አንድ ሺህ 359 ተማሪዎች በመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ ዛሬ አስመርቋል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት አስማረ መለሰ (ዶ/ር ) በስነ ስርአቱ ላይ ባስተላለፉት መልእክት ዩኒቨርሲቲው የፈጠራና የቴክኖለጂ ሽግግርን ለማረጋገጥ በእውቀትና በክህሎት የጎለበተ የሰው ሀይል እያፈራ ይገኛል።
በአካባቢው እያደገ የመጣውን የኢንዱስትሪና የኢንቨስትመንት መስፋፋት በተማረ የሰው ሃይል አቅርቦት ለማገዝ የዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ አማካሪ ቦርድ በማቋቋም እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህም ተማሪዎች በኢንዱስትሪዎች የተግባር ልምምድ በማድረግ ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩና የኢንዱስትሪዎችንም የማምረት አቅም የሚያሳድግ መሆኑን አመልክተዋል።
ዩኒቨርሲቲው በዛሬው እለት በመደበኛና ተከታታይ መርሀግብር ያሰለጠናቸውን አንድ ሺህ 359 ተማሪዎች ዛሬ ማስመረቁን ተናግረዋል።
ከተመራቂዎች መካከል 431ዱ ሴቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ተመራቂዎች በቆይታቸው በቀሰሙት እውቀትና ክህሎት በመጠቀም የአገሪቱን እድገት ለማፋጠን እንዲተጉ አሳስበዋል።
በምረቃ ስነ ስርአቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጀኔራል ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ሀይሉ ተመራቂዎች በሚሰማሩበት የስራ መስክ ሁሉ ታታሪና ትጉህ በመሆን እንዲሁም አዳዲስ ፈጠራ ላይ በማተኮር የተጀመረውን ልማትና ሰላም በማፋጠን የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ አመልክተዋል።
ከቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል አራት ነጥብ በማምጣት የወርቅ ሜዳሊያና የዋንጫ ተሸላሚ የሆነችው ፈትያ አህመድ እንደገለጸችው በተመረቀችበት ሙያ ከአድሎአዊ አሰራር በፀዳ መልኩ ህዝብን ለማገልገል መዘጋጀቷን ተናግራለች ።
"ዜጎች ፍትህን በእኩልነትና ፍትሃዊነት እንዲያገኙ እሰራለሁ" ያለው ደግሞ ከህግ ትምህርት ክፍል 3 ነጥብ 94 በማምጣት የሜዳሊያ ተሸላሚ የሆነው ጋሻው ሽቶ ነው።