የፕሪሚየር ሊጉ የመጨረሻ ሳምንት መርሃ ግብር ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
የፕሪሚየር ሊጉ የመጨረሻ ሳምንት መርሃ ግብር ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳል
አዲስ አበባ ፤ ሰኔ 15/2017 (ኢዜአ) ፡- የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 36ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ዛሬ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ይጀመራል።
ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ኢትዮጵያ ቡና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ይጫወታሉ።
ኢትዮጵያ ቡና በ59 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል። በሊጉ ሁለተኛ ደረጃን ይዘው ማጠናቀቃቸውን ያረጋገጡት ቡናማዎቹ ካሸነፉ በሊጉ 18ኛ ድላቸውን ያስመዘግባሉ።
የአምናው የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ43 ነጥብ 11ኛ ደረጃን ይዟል። ቡድኑ በ35ኛ ሳምንት ሀድያ ሆሳዕናን በማሸነፍ በሊጉ መቆየቱን ማረጋገጡ የሚታወስ ነው።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመቻል ምሽት 12 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
የ16 ጊዜ የሊጉ አሸናፊ የሆነው ቅዱስ ጊዮርጊስ በ45 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ መቻል በ44 ነጥብ 9ኛ ደረጃን ይዟል።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጨረሻ የ36ኛ ሳምንት መርሃ ግብር እስከ ሰኔ 19 ቀን 2017 ዓ.ም ይቆያል።