ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ያደረግነው ውይይት መንግሥት ከተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ ጋር በትብብር ለመሥራት ያለውን ቁርጠኝነት ያረጋገጥንበት ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 15/2017(ኢዜአ)፦ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር ያደረግነው ውይይት መንግሥት ከተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ ጋር በትብብር ለመሥራት ያለውን ቁርጠኝነት ማጠናከሩን ያረጋገጥንበት ሲሉ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ገለጹ።

ውይይቱ የዴሞክራሲ ባህልን በማዳበር ረገድም ትልቀ ሚና እንዳለው አንስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሰኔ 11/2017 ዓ.ም ከመላው ሀገሪቱ ከተወጣጡ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ጋር ውይይት ማድረጋቸው ይታወቃል።

ውይይቱን አስመልክተው አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት የኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ህብረት ፀሐፊ ዙሪያሽ ሰይድ በውይይቱ መሳተፋቸውን ገልፀው ከለውጡ በፊት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከሀገር መሪ ጋር ተገናኝቶ የመወያየት ዕድል እንዳልነበራቸው ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ ሀገርን መገንባት የሚቻለው በጋራ ነው በሚል እሳቤ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በተደጋጋሚ ጊዜ እየተወያዩ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህም መንግሥት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገር ሰላምና ልማት ላይ የበኩላቸውን እንዲወጡ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።

የቅማንት ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ምክትል ሊቀ መንበር ተገኑ ደረጀ ውይይቱ መንግስት ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ምህዳርን ለማስፋት ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር ያረጋገጠበት ነው ብለዋል።

መንግስት ሀገር መገንባት የሚቻለው በትብብር ነው በሚል እሳቤ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመቀራረብ እየሰራ ያለው ስራ አበረታች እና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት እንደሆነ ተናግረዋል።

የአርጎባ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት የሥራ አስፈፃሚ አባል ሸሚስያ መሐመድ ሱሩር በበኩላቸው፥ ውይይቱ መንግስት ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በትብብር ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑን ያረጋገጥንበት ነው ብለዋል።

ውይይቱ በኢትዮጵያ ያለው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ገንቢ ፉክክርንና ትብብርን መሰረት ያደረገ እንዲሆን የሚያስችል ነው ያሉት ደግሞ የትንሳኤ ሰብዓ እንደርታ ፓርቲ ሊቀ መንበር ከበደ አሰፋ ናቸው።

በጋራ ሀገራዊ ጉዳዮች ተቀራርቦ ከመስራት አኳያም የለውጡ መንግሥት በቀደሙት መንግሥታት ያልታየ ተነሳሽነት መውሰዱን አንስተዋል።

ውይይቱ ከለወጡ ወዲህ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በትብብር ለሀገረ መንግሥት ግንባታ በጎ ሚና እንዲጫወቱ የተከፈተውን ምህዳር የሚያጠናክር መሆኑንም አመራሮቹ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም