ቀጥታ፡

ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ በሀሳብ ላይ የተመሰረተ የዴሞክራሲ ባህል እየዳበረ ነው-የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባላት

አዲስ አበባ፤ሰኔ 14/2017 (ኢዜአ) :-ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ በመተባበርና በሀሳብ ፉክክር ላይ የተመሰረተ የዴሞክራሲ ባህልና ልምምድ እየዳበረ መምጣቱን የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባላት ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሰኔ 11 ቀን 2017 ዓ.ም ከሁሉም የሀገሪቱ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች ጋር በሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸው ይታወቃል።

ከውይይቱ ማግስት የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባላት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተገነቡና በግንባታ ሂደት የሚገኙ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል።

በብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ባህል ግንባታና የምርጫ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አሸብር ታደሠ (ዶ/ር)፥ ከሀገራዊ ለውጡ ማግስት የተፎካካሪ ፓርቲ አመራር አባላት በሀገራቸው ጉዳይ በትብብር የሚሰሩበት አካታች የፖለቲካ ምኅዳር መፈጠሩን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በሁላችንም ትብብር የምትገነባ ሀገር ናት ያሉት ኃላፊው፥ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራር አባላት በመንግሥት መዋቅር ስልጣን ይዘው ሀገራቸውን የሚያገለግሉበት አካታች ዕድል ተፈጥሯል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ የክልልና ከተማ አስተዳደር የስራ ኃላፊዎች ከተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች ጋር የሚያደርጉት ምክክርም ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የማይተካ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

የአፋር ነፃ አውጪ ግንባር ፓርቲ ምክትል ሰብሳቢ ሀጂ እስማዔል መሀመድ፥ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አመራር የተፈጠረው አዲስ የፖለቲካ ባህል የሀገርን ዕድገት ለማስቀጠል መሰረት የጣለ ነው ብለዋል።

በተለያየ አደረጃጀቶች የሚደረጉ የምክክር መድረኮች አዲስ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ምኅዳር ስለመፈጠሩ ተጨባጭ ማሳያዎች እንደሆኑም ገልጸዋል።

የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ የወጣቶች ክንፍ ኃላፊ ጥጋቡ ደጀኔ÷ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የፈጠሩት መድረክ ስልጡንና በሀሳብ ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ምኅደርን በማስፋት ለሀገር ዕድገት መተባበር እንደሚገባ ያሳየ ነው ብለዋል።

በጋምቤላ ክልል የኢዜማ ምክትል መሪ ጋትቤል ቦል÷ ከሀገራዊ ለውጡ በፊት የተፎካካሪ ፓርቲ አመራር አባላት ከገዥው ፓርቲና ከመንግስት ጋር በትብብር የመስራት ባህል እንዳልነበር አውስተዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሚመራው የለውጡ መንግሥት የተፎካካሪ ፓርቲ አባላት በፌደራልና በክልል መንግስታት የካቢኔ አባል በመሆን ሀገራቸውን እንዲያገለግሉ ዕድል መፈጠሩን ገልጸዋል።

የአፋር ነፃ አውጪ ግንባር ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ መሐመድ አይዲያይስ÷ ከዚህ ቀደም የነበረው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል አንዱ የሰራውን ሌላው የማፍረስ አባዜ የተጠናወተው ነበር ብለዋል።

ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሚችለው ሁሉ ለሀገር ዕድገት አዎንታዊ አስተጽኦ የሚያበረክትበት በመማማር ላይ የተመሰረተ አዲስ የፖለቲካ ምኅዳርና የዴሞክራሲ ልምምድ መፈጠሩን አንስተዋል።

በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ ገለታ ኃይሉ÷ በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ለዘላቂ ሰላምና ለልማት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም