በንድፈ ሀሳብና በተግባር በቀሰምነው እውቀት ለሀገራችን ሰላምና ልማት እንሰራለን - ተመራቂ የፖሊስ መኮንኖች - ኢዜአ አማርኛ
በንድፈ ሀሳብና በተግባር በቀሰምነው እውቀት ለሀገራችን ሰላምና ልማት እንሰራለን - ተመራቂ የፖሊስ መኮንኖች

አዲስ አበባ፤ሰኔ 14/2017 (ኢዜአ)፦በንድፈ ሀሳብና በተግባር በቀሰምነው እውቀት ለኢትዮጵያ ሰላምና ልማት እንሰራለን ሲሉ የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ የፖሊስ መኮንኖች ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ መስኮች ከመደበኛ ሰርተፊኬት እስከ ሁለተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ በተገኙበት አስመርቋል፡፡
የፖሊስ መኮንኖች በሁለተኛ ዲግሪ፣ በመጀመሪያ ዲግሪ፣ በሌቭል አራትና በጤና ሳይንስ እንዲሁም በሌሎች የትምህርት ዘርፎች የሰለጠኑ ናቸው፡፡
ኢዜአ ያነጋገራቸው ተመራቂዎች በትምህርት ቆይታቸው ወንጀልን መከላከልና በሳይንሳዊ መንገድ መመርመር የሚያስችል ጥልቅ እውቀት ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡
በሚሰማሩበት የሙያ መስክ ዜጎችን በታማኝነትና በቅንነት ለማገልገል መዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል፡፡
ከዩኒቨርሲቲው በወንጀል ምርመራ የትምህርት መስክ በወንጀል ምርመራ አድቫንስ ዲግሪ የተመረቀችው ሰልጣኝ መኮንን ክብረዓለም አስፋው በሰጠችው አስተያየት፤ በትምህርቷ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ለመድረስ ጥረትና ችግሮችን ተቋቁሞ የማለፍ ብቃት እንዳገዟት ተናግራለች፡፡
ፖሊስ እየታጠቀ የሚገኘውን ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ከቀሰመችው እውቀት ጋር በማጣመር በወንጀል ምርመራ ዘርፍ የሚጠበቅባትን ኃላፊነት ለመወጣት መዘጋጀቷን ገልጻለች፡፡
የሴኩሪቲ ሴክተር ማኔጀመንት ትምህርት መስክ ተመራቂ ኢንስፔክተር አሸናፊ ዓለማየሁ በበኩላቸው፥ የወንጀል መከላከልና ምርመራ ሥራን በአግባቡ መወጣት የሚያስችላቸውን ዕውቀት መቅሰማቸውን ተናግረዋል፡፡
የፖሊስን ዋና ተግባር በጀግንነት መጠበቅና በሰብዓዊነት ማገልገል የሚለውን መርህ በብቃት ለመወጣትና በቅንነት ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
ሌላኛው ተመራቂ ረዳት ኢንስፔክተር ተረፈ ጪምዴሳ በትምህርት ባገኙት እውቀት ሀገርን ለማገልገል መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸውም ብቃት ያለው የንድፈ ሐሳብና የተግባር ትምህርት መከታተላቸውን ጠቁመው በዚህም ህዝብን በታማኝነት እንደሚያገለግሉ ገልጸዋል፡፡
ረዳት ኢንስፔክተር አህመድ ኢብራሂም በበኩላቸው ፖሊሳዊ ሙያ ከራስ በላይ ለሕዝብ ሰላምና ድኅንነት ቅድሚያ መስጠት በመሆኑ በቅንነትና በታማኝነት ሕዝቡን ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ሕብረተሰቡ የሚፈልገውን የወንጀል መከላከልና ምርመራ ሥራን በአግባቡ ለመወጣትም ዝግጁ ነኝ ብለዋል፡፡