ፖሊስ ህብረተሰቡን በሙያዊ ስነምግባር በማገልገል ህዝባዊነቱን አፅንቶ መቀጠል አለበት - ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ - ኢዜአ አማርኛ
ፖሊስ ህብረተሰቡን በሙያዊ ስነምግባር በማገልገል ህዝባዊነቱን አፅንቶ መቀጠል አለበት - ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ
አዲስ አበባ፤ሰኔ 14/2017 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ፖሊስ አመራርና አባላት ሀገርና ህዝብን በታማኝነትና በሙያዊ ስነምግባር በማገልገል ህዝባዊነታቸውን አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ መስኮች ከመደበኛ ሰርተፊኬት እስከ ሁለተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች አስመርቋል።
የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ የዕለቱ ምሩቃን ፍሬያማ ጊዜን በማሳለፍ ለምረቃ በመብቃታቸው እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
ኢትዮጵያ የረጅም ዘመናት የነጻነት ታሪክ ያላት መሆኗን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ የኢትዮጵያዊነት ምሰሶና ካስማም ተጠብቆ መኖሩን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እጅግ ዘመናዊና በዓለም አቀፍ እንዲሁም በአህጉር ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ፤ በሙያና በህዝብ አገልግሎት የተመሰከረለት ተቋም እንዲሆን ይዞት የተነሳው ራዕይ የሚመሰገን ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጊዜው የሚጠይቀውን የወንጀል መከላከልና የምርመራ ስራን በቴክኖሎጂ ላይ ተመስርቶ ማከናወን የሚችል ብቃትና አቅም ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ብቃት ያለው የሰው ኃይል ለማፍራት ማህበረሰቡን የሚያሳትፍ አዳዲስ የፖሊስ ቴክኖሎጂዎችን ለመጠቀም የጀመረውን ተግባር አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ግልጽ፣ ንጹህና የህዝብ አገልጋይ መሆኑን በማረጋገጥ ላይ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡
ዘላቂ ሰላምን ማጽናት የሁሉም ሃላፊነት መሆኑን በማንሳት የህዝቡን ሰላም የሚያውኩ አካላትን ወደ ምክክር ማምጣት እንዲሁም የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ፖሊሳዊ ሙያንና ስነምግባርን በመላበስ ሁልጊዜም ህብረተሰቡን በክብርና በሰብዓዊነት በማገልገል ህዝባዊነትን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ለጎረቤት ሀገራት እየሰጠ ያለው የነጻ የትምህርት ዕድል ሽብርተኝነትን እና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በጋራ ለመከላከል የተጀመረውን ጥረት እንደሚያጠናክርም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል እንዳሉትም፤ ዩኒቨርሲቲው በሙያዊ እውቀትና በስነ-ምግባር የታነጹ ብቁ ሰልጣኞችን ለማፍራት የተጣለበትን ኃላፊነት በሚገባ እየተወጣ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ እያደገ ለመጣው ፖሊሳዊ አገልግሎት ይበልጥ መጠናከር የበኩሉን እየተወጣ መሆኑንም አንስተዋል።
ዩኒቨርሲቲው የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት የፖሊስ ተልዕኮን የመፈጸም አቅም ለማሳደግ ዘመኑን በዋጀ ሙያዊ እውቀት ብቁ ሰልጣኞችን ከማፍራት አኳያ አመርቂ ስራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መስፈን አበበ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ሪፎርም በማድረግ ብቁ የሰው ኃይል የማፍራት ሀገራዊ ሃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲው የፖሊስ ትምህርትና ስልጠና ጥራቱን የጠበቀ በማድረግ ትልቅ ሥራ እያከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል።
ሰልጣኞች ዘመኑን የዋጀ እውቀት እንዲቀስሙ በስድስት የሁለተኛ ዲግሪ፣ በ19 የመጀመሪያ ዲግሪ መርሐ ግብር እና በሌሎች የትምህርት መስኮች በማስተማር ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።