ቀጥታ፡

የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርሙ ለዜጎች ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ ፤ሰኔ 14/2017 (ኢዜአ)፦የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርሙ ለዜጎች ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡

10ኛው የአፍሪካ የፐብሊክ ሰርቪስ ቀን "የሲቪል ሰርቪስ ተቋማትን ቅልጥፍና እና ጽናትን በማሳደግ በታሪክ አጋጣሚ የተፈጠሩ የአገልግሎት አሰጣጥ ክፍተቶችን መሙላት" በሚል መሪ ሀሳብ በአፍሪካ ሕብረት መሰብሰቢያ አዳራሽ መካሄድ ጀምሯል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በዚህ ወቅት፥ የአፍሪካ ሲቪል ሰርቪስ ቀን ጠንካራ ተቋማትን ለመገንባት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።


የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደርን ማሻሻል የአፍሪካ ሕብረት አጀንዳ 2063ን እና የዘላቂ ልማት ግቦችን ማሳካት የሚያስችል ነው ብለዋል።

አካታች፣ ፍትሐዊና ቀልጣፋ የጤና፣ የትምህርት፣ የፍትህ አገልግሎት ለመስጠት  የሰው ኃይል አስተዳደር ስርዓቱን ማዘመን እንደሚገባም ተናግረዋል።

ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት ማለት ያልዘገየ ምላሽ መስጠት መሆኑን በመጥቀስ፣ ግልጽና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ስርዓትን በመገንባት በታሪክ አጋጣሚ የተፈጠረውን የአገልግሎት አሰጣጥ ስብራት መጠገን ይገባል ብለዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ ወረርሽኝ እና ግጭት የዓለም ፈተናዎች መሆናቸውን ገልጸው፤ አፍሪካ ችግሮችን ለመቋቋም ጠንካራ የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም በመገንባት ቀልጣፋና ፍትሐዊ አገልግሎት መስጠት እንዳለባት ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በሰባት መርሆዎች ላይ የተመሰረተ ሁሉን አቀፍ የመንግሥት አገልግሎትና አስተደደር ሪፎርም እያደረገች መሆኗን በመጥቀስ ተጨባጭ ውጤት በማስመዝገብ ላይ ናት ብለዋል፡፡

በተለይም የሪፎርሙ መሰረታዊ አንጓ የሆነው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የመንግስትን አገልግሎት አሰጣጥ ቀልጣፋና ዘመናዊ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የመንግስትን የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት ዘመናዊና ቀልጣፋ በማድረግ የአሰራር ባህልን መቀየሩን አንስተዋል፡፡


 

መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መንግሥት ለህዝቡ የበለጠ እንዲቀርብ ማድረጉን አስረድተው፤ ዜጎች በስልካቸውም ሆነ በአካል ሁሉንም መንግስታዊ አገልግሎቶች በአንድ ቦታ እንዲያገኙ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ በሁሉም አካባቢዎች የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ለማስፋት እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፣ ይህም ለሁሉም ዜጎች ቀልጣፋ የመንግስት አገልግሎት መስጠት እንደሚያስችል ጠቁመዋል።

በአፍሪካ ጠንካራ የሲቪል ሰርቪስ ተቋማትን በመገንባት ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት አፍሪካውያን በትብብር መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

የአፍሪካ የፐብሊክ ሰርቪስ ቀን የመንግስት ተቋማት ተለዋዋጭ ከባቢያዊ ሁኔታዎችን በመቋቋም ለብዙ ጊዜያት እየተንከባለሉ የመጡና ከአገልግሎት ጋር ለተያያዙ ፈተናዎች በፍጥነት መፍትሔ ለማበጀት ትኩረት ያደረገ ነው።


 

በአፍሪካ የተከማቹ የአገልግሎት አቅርቦት ችግሮችን በመፍታት አካታች፣ ዘላቂ ልማት የሚያመጣ፣ ተጠያቂነትን የሚያሰፍን፣ የሰብዓዊ መብትን የሚያከብር፣ የህዝቦችን ትስስር የሚያጠናክር ጠንካራ ተቋም መገንባት የሚያስችል መድረክ መሆኑም ተገልጿል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም