ቀጥታ፡

ምሩቃን በገበያችሁት እውቀት ህዝብን እና ሀገርን በቅንነት፣ በታማኝነትና በታታሪነት ለማገልገል መዘጋጀት አለባችሁ- ተስፋዬ ቤልጅጌ (ዶ/ር)

ወራቤ ፡ ሰኔ 14/2017 (ኢዜአ) ምሩቃን በትምህርት ቆይታችሁ በገበያችሁት እውቀት ህዝብን እና ሀገርን በቅንነት፣ በታማኝነትና በታታሪነት ለማገልገል መዘጋጀት አለባችሁ ሲሉ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጂጌ ገለጹ፡፡ 

የወራቤ ዩኒቨርሲቲ ለ6ኛ ዙር በተለያዩ የትምህርት አይነቶች ያሰለጠናቸውን 1 ሺህ 561 ተማሪዎች አስመርቋል፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጅጌ (ዶ/ር)፤ የትምህርት ዘርፉ ለሀገር ግንባታ፣ ህብረ ብሄራዊ አንድነትና ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ መሰረት መሆኑን ገልጸዋል።


 

የኢትዮጵያን የትምህርት ስብራት በመጠገን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እና እውቀት መር በሆነ መልኩ እንዲገነባ በለውጡ ሰፊ የሪፎርም ስራ መከናወኑን አንስተዋል።

በዚህም የሚታይ ውጤትና ተጨባጭ ለውጥ መምጣቱን ጠቅሰው የትምህርት ዘርፉን ይበልጥ በማጠናከር በእውቀት የበቃ ለሀገር ልማት እድገትና ብልጽግና መሰረት የሚያኖር ትውልድ የመገንባት ስራ በተጠናከረ መልኩ ይቀጥላል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በብዙ ተስፋና ውጤት ወደፊት እየተራመደች መሆኑን የገለጹት ዶክተር ተስፋዬ፤ በዚህ ረገድ ተመራቂ ተማሪዎች ድርብ ሃላፊነት አለባችሁ ያሉ ሲሆን ከራስ ባለፈ ለቤተሰብ፣ ለህዝብና ለሀገር በቅንነት፣ በታማኝነትና በታታሪነት ለማገልገል መዘጋጀት አለባችሁ ሲሉም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ የአሁን ችግሮች ለዘመናት እየተንከባለሉ የመጡ ስብራቶች መሆናቸውን ጠቅሰው በሁሉም ረገድ ችግሮችን በማለፍ የሀገር እድገትና ብልጽግናን ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የወራቤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ኢንጂነር ቶፊቅ ጀማል (ዶ/ር) ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ባለፈ በምርምርና በማህበረሰብ አገልግሎት ኃላፊነቱን በብቃት እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ከተለያዩ የትምህርት ተቋማት ጋር በመተባበር በትምህርትና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች በቅርበት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው ይህም በተጠናከረ መልኩ የሚቀጥል መሆኑንም አረጋግጠዋል።

ከዩኒቨርሲቲው የተመረቁ ተማሪዎችም የቀሰሙትን እውቀት ወደ ተግባር በመለወጥ ከራስ አልፎ ለሀገርና ለህዝብ የሚጠቅም አስተዋጽኦ ማድረግ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

በዩኒቨርሲቲው ከማኔጅመንት ትምህርት ክፍል አጠቃላይ የዋንጫ ተሸላሚ የሆነችው ኢክራም ሀይሉ በዩኒቨርሲቲ ቆይታዋ ያገኘችውን እውቀትና የላቀ ውጤት ለሀገርና ለህዝብ በሚጠቅም መልኩ ለመተግበር ተዘጋጅቻለሁ ብላለች።


 

በጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት በከፍተኛ ማዕረግ የተመረቀችው ሊድያ አለማየሁ፤ የሀገርን ጥቅም በማስቀደም በመረጃ ተደራሽነትና እውነታን በማሳወቅ ረገድ የድርሻዋን ለማበርከት መዘጋጀቷን ተናግራለች።


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም