የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ በሙያዊ እውቀትና በስነ ምግባር የታነጹ ብቁ ሰልጣኞችን እያፈራ ነው-ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ በሙያዊ እውቀትና በስነ ምግባር የታነጹ ብቁ ሰልጣኞችን እያፈራ ነው-ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል
አዲስ አበባ፤ሰኔ 14/2017 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ በሙያዊ እውቀትና በስነ-ምግባር የታነጹ ብቁ ሰልጣኞችን ለማፍራት የተጣለበትን ኃላፊነት በሚገባ እየተወጣ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ።
የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ መስኮች ያሰለጠናቸውን ሰልጣኞችን አስመርቋል።
ተመራቂዎች ከመደበኛ ሰርተፊኬት እስከ ማስተርስ ዲግሪ ድረስ ስልጠናቸውን የተከታተሉ ናቸው ተብሏል።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በዚሁ ወቅት፤የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ በፖሊሳዊ ሙያ የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት ላይ ይገኛል ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲው ከሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች እና ከጎረቤት ሀገራት ለተወጣጡ ሰልጣኞች ስልጠና በመስጠት የመፈጸምና የማስፈጸም አቅምን እያሳደገ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የፖሊስ የኢኖቬሽን እና የቴክኖሎጂ ማዕከል በቅርቡ ወደ ስራ እንደሚገባ ጠቁመው ፖሊስን በቴክኖሎጂና በሌሎችም ግብዓቶች የማጠናከር ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ እያደገ ለመጣው ፖሊሳዊ አገልግሎት ይበልጥ መጠናከር የበኩሉን እየተወጣ መሆኑንም አንስተዋል።
ዩኒቨርሲቲው የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት የፖሊስ ተልዕኮን የመፈጸም አቅም ለማሳደግ ዘመኑን በዋጀ ሙያዊ እውቀት ብቁ ሰልጣኞችን ከማፍራት አኳያ አመርቂ ስራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ፖሊስ የሀገርን ሰላምና ልማት ለማጽናትና የሁልጊዜም ግዳጁን ለመወጣት በአስተማማኝ ቁመና ላይ መሆኑን አረጋግጠዋል።
ተመራቂዎች ባገኙት ዕውቀት ሀገራቸውን በታማኝነትና በስነ-ምግባር ማገልገል እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
በመርቃ መርሐ ግብሩ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ፣ የስራ እና ክህሎት ሚኒስትርና የዩኒቨርሲቲው የቦርድ ሰብሳቢ ሙፈሪያት ካሚልን ጨምሮ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከፍተኛ አመራሮች፣ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት፣የፖሊስ መኮንኖች፤ የተመራቂ ቤተሰቦችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።