ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የአሰራር ባህል ለውጥና ተጨባጭ ውጤት እያመጣች ነው-ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

 

አዲስ አበባ፤ሰኔ 14/2017 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በመጀመር የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን የአሰራር ባህል ለውጥና ተጨባጭ ውጤት እያመጣች መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

በአፍሪካ ጠንካራ የሲቪል ሰርቪስ ተቋማትን ለመገንባትም አህጉራዊ ትብብር ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

10ኛው የሲቪል ሰርቪስ ቀን "የሲቪል ሰርቪስ ተቋማትን ቅልጥፍና እና ጽናትን በማሳደግ በታሪክ አጋጣሚ የተፈጠሩ የአገልግሎት አሰጣጥ ክፍተቶችን መሙላት" በሚል መሪ ሀሳብ በአፍሪካ ሕብረት መሰብሰቢያ አዳራሽ መካሄድ ጀምሯል።


 

ስብሰባው የመንግስት ተቋማት ተለዋዋጭ ከባቢያዊ ሁኔታዎችን በመቋቋም ለብዙ ጊዜያት እየተንከባለሉ የመጡና ከአገልግሎት ጋር ለተያያዙ ፈተናዎች በፍጥነት መፍትሔ ለማበጀት ትኩረት ያደረገ ነው።

በአፍሪካ የተከማቹ የአገልግሎት አቅርቦት ችግሮችን በመፍታት አካታች፣ ዘላቂ ልማት የሚያመጣ፣ ተጠያቂነትን የሚያሰፍን፣ የሰብዓዊ መብትን የሚያከብር፣የህዝቦችን ትስስር የሚያጠናክር ጠንካራ ተቋም መገንባት የሚያስችል መድረክ መሆኑም ተገልጿል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በዚህ ወቅት፥ የአፍሪካ ሲቪል ሰርቪስ ቀን ጠንካራ ተቋማትን ለመገንባት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደርን ማሻሻል የአፍሪካ ሕብረት አጀንዳ 2063ን እና የዘላቂ ልማት ግቦችን ማሳካት የሚያስችል ነው ብለዋል።

አካታች፣ፍትሐዊና ቀልጣፋ የጤና፣ የትምህርት፣ የፍትህ አገልግሎት ለመስጠት የሰው ኃይል አስተዳደር ስርዓቱን ማዘመን እንደሚገባም ተናግረዋል።


 

ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት ማለት ያልዘገየ ምላሽ መስጠት መሆኑን በመጥቀስ፣ ግልጽና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ስርዓትን በመገንባት በታሪክ አጋጣሚ የተፈጠረውን የአገልግሎት አሰጣጥ ስብራት መጠገን ይገባል ብለዋል።

ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ ሀገራዊ ሪፎርም በማድረግ ተጨባጭ እርምጃ መውሰዷን አንስተዋል ።

የአገልግሎት አሰጣጡን ቀልጣፋና ዘመናዊ ማድረግ የሚያስችል መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጠት መጀመሯን ገልጸዋል።

የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የመንግስትን የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት ዘመናዊና ቀልጣፋ በማድረግ የአሰራር ባህልን የሚቀይር መሆኑን ተናግረዋል።


 

በኢትዮጵያ በሁሉም አካባቢዎች የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ለማስፋት እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፣ ይህም ለሁሉም ዜጎች ቀልጣፋ የመንግስት አገልግሎት መስጠት እንደሚያስችል ጠቁመዋል።

በአፍሪካ ጠንካራ የሲቪል ሰርቪስ ተቋማትን በመገንባት ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት አፍሪካውያን በትብብር መስራት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም