ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፖሊስ ዘላቂ ሰላምን የማስጠበቅና ወንጀልን የመከላከል ተልዕኮውን በብቃት መፈጸም የሚያስችል አቅም ገንብቷል - ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ


አዲስ አበባ፤ሰኔ 14/2017 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ፖሊስ ወንጀልን በመከላከል የሀገር እና የህዝብን ዘላቂ ሰላም የማስጠበቅ ተልዕኮውን  በብቃት መፈጸም የሚያስችል የሰው ኃይልና  ዘመኑን የዋጀ የቴክኖሎጂ አቅም መገንባቱን የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ መስኮች ከመደበኛ ሰርተፊኬት እስከ ሁለተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች አስመርቋል።


 

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ የዕለቱ ምሩቃን ፍሬያማ ጊዜን በማሳለፍ ለምረቃ በመብቃታቸው እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።

ኢትዮጵያ የረጅም ዘመናት የነጻነት ታሪክ ያላት መሆኗን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ የኢትዮጵያዊነት ምሰሶና ካስማም ተጠብቆ መኖሩን ተናግረዋል።

የሀገርን ሰላምና የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ የሁሉም ሃላፊነት መሆን እንዳለበት ጠቁመው ፖሊስም ይህን ሀገራዊ ሃላፊነቱን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያን ሰላም በማጽናት የስልጣኔ ማዕከልነቷን ማስቀጠል እንደሚገባ ጠቁመው ለዘመናት የተገነቡ መልካም ዕሴቶችን ጠብቆ ማስቀጠልም ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ዘላቂ ሰላምን ማጽናት የሁሉም ሃላፊነት መሆኑን በማንሳት የህዝቡን ሰላም የሚያውኩ አካላትን ወደ ምክክር ማምጣት እንዲሁም የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ እንደሚገባ ተናግረዋል።


 

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጠንካራ እና ተወዳዳሪ ተቋም ለመሆን የጀመራቸው ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የወንጀል መከላከል እና ምርመራውን ለማከናወን የጀመራቸው ስራዎች የሀገርን ዘላቂ ሰላም ለማጽናት ምቹ መደላድል የሚፈጥሩ ናቸው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ለጎረቤት ሀገራት እየሰጠ ያለው የነጻ የትምህርት ዕድል ሽብርተኝነትን እና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በጋራ ለመከላከል የተጀመረውን ጥረት እንደሚያጠናክርም ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ በርካታ መሠረተ ልማቶች እየተገነቡ መሆናቸውን ያነሱት ፕሬዚዳንቱ ፖሊስ መሰረተ ልማቶችን ከህብረተሰቡ ጋር በመጠበቅ ለረጅም ዓመት ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡ ማስቻል አለበት ብለዋል። 

ከተመራቂዎች መካከል የጎረቤት ሀገራት ተማሪዎች ይገኙበታል ተብሏል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም