የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች እያስመረቀ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች እያስመረቀ ነው
አዲስ አበባ ፤ሰኔ 14/2017(ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ከመደበኛ ሰርተፊኬት እስከ ሁለተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች በማስመረቅ ላይ ይገኛል።
በምርቃት ስነ ስርዓቱ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ፣ የስራ እና ክህሎት ሚኒስትርና የዩኒቨርሲቲው የቦርድ ሰብሳቢ ሙፈሪሃት ካሚል፣ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፣ የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርስቲ አመራሮች፣ የፖሊስ መኮንኖች፣ የተመራቂ ቤተሰቦችን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።
የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መስፈን አበበ ባደረጉት ንግግር፤ የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ሪፎርም በማድረግ ብቁ የሰው ኃይል የማፍራት ሀገራዊ ሃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል። ዩኒቨርሲቲው የፖሊስ ትምህርትና ስልጠና ጥራቱን የጠበቀ በማድረግ ትልቅ ሥራ እያከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል።
ሰልጣኞች ዘመኑን የዋጀ እውቀት እንዲቀስሙ በስድስት የሁለተኛ ዲግሪ፣ በ19 የመጀመሪያ ዲግሪ መርሐ ግብር እና በሌሎች የትምህርት መስኮች በማስተማር ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ለጎረቤት ሀገራት ተማሪዎችም ነጻ የትምህርት ዕድል በመስጠት ለቀጣናዊ ትብብር መጠናከር ጉልህ ሚና እየተወጣ ነው ብለዋል።