ቀጥታ፡

በክልሉ የኢትዮ ኮደርስ ሥልጠና በውጤታማነት ተጠናክሮ ቀጥሏል

ሆሳዕና፤ ሰኔ 14/2017(ኢዜአ)፡-  በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የኢትዮ  ኮደርስ ሥልጠና  በውጤታማነት ተጠናክሮ መቀጠሉን   የክልሉ የሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ገለጸ ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዜጎች በዌብ ፕሮግራሚንግ፣ በአንድሮይድ ማበልፀግ፣ ዳታ ሳይንስና አርተፊሻል ኢንተለጀንሥ መሰረታዊ የዲጂታል ክህሎት እንዲኖራቸው ለማስቻል የኢትዮ ኮደርስ ሥልጠና በሐምሌ ወር 2016 ዓ.ም ማስጀመራቸው ይታወሳል። 


 

በዚህም በርካታ ወጣቶች አቅማቸውን ለማሳደግና ዘመኑን የዋጀ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ለመሆን  ሥልጠናውን በ"ኦን ላይን"  እየተከታተሉ ነው። 

የሥልጠናው መረሃ ግብር ተጠናክሮ በውጤታማነት ከቀጠለባቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች  ውስጥ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ይገኝበታል። 

የክልሉ የሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ  ኃላፊ አቶ ሰላሙ አማዶ  እንደገለጹት፤ እየተገባደደ ባለው  የበጀት ዓመት ከ49 ሺህ በላይ ዜጎችን በኢትዮ ኮደርሥ ሥልጠና ለማሳተፍ ታቅዶ  60 ሺህ  ዜጎችን በማሰልጠን ከዕቅድ በላይ ማከናወን ተችሏል፡፡


 

በዲጂታል ቴክኖሎጂ የበቁ ዜጎችን ለማፍራት መንግሥት በሰጠው ትኩረትም የኮደርስ  ሥልጠናውን  ከወሰዱት  ውስጥ ከ 38 ሺህ በላይ ዜጎች የእውቅና የምስክር ወረቀት ማግኘታቸውን  ጠቅሰዋል፡፡

የእውቅና ምስክር ወረቀቱ ዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያለው በመሆኑ የሥራ እድልን ለዜጎች  እንደሚከፍትም አንሥተዋል፡፡

የኢትዮ ኮደርስ ሥልጠናው ሰልጣኞችን  ከዲጂታል ዓለም ጋር በመቀላቀል በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንደሚያደርግ የገለጹት ደግሞ በሆሳዕና ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የፋሽን ዲዛይን አሰልጣኝ መምህር ዳዊት ከበደ  ናቸው።


 

ሰልጣኞች  በአንድሮይድ ማበልፀግና የዳታ ሳይንስ ላይ ተወዳዳሪ የሚያደርጋቸውን ክህሎት በመቅሰም   የምስክር  ወረቀት  ማግኘት እንደሚያስችልም  ተናግረዋል፡፡

ይህም የዲጂታል ዓለምን በመቀላቀል የተለያዩ የሥራ እድሎችን ተጠቃሚ ማድረግ  እንደሚያስችል አስረድተዋል፡፡

በኮሌጁ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ትምህርት ክፍል የ3ኛ ዓመት ተማሪ ኤልሳቤጥ ግርማ በሰጠችው አስተያየት፤  የኢትዮ ኮደርስ ሥልጠና  በመውሰዷ ራሷን  በቴክኖሎጂው ዘርፍ ብቁና ተወዳዳሪ መሆን   እንዳስቻላት ተናግራለች፡፡


 

ሥልጠናው በተለይ ለወጣቶች የሥራ ፈጠራ  በር የሚከፍት በመሆኑ ባገኘችው እውቀት የራሷን ሥራ ለመፍጠር  እንደምትጥር ገልጻለች ፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም