ቤኔፊካ በኦክላንድ ሲቲ ላይ ግማሽ ደርዘን ጎል በማስቆጠር አሸንፏል - ኢዜአ አማርኛ
ቤኔፊካ በኦክላንድ ሲቲ ላይ ግማሽ ደርዘን ጎል በማስቆጠር አሸንፏል
አዲስ አበባ ፤ ሰኔ 14/2017(ኢዜአ):- በፊፋ ክለቦች የዓለም ዋንጫ በምድብ ሶስት በተካሄደ ጨዋታ ቤኔፊካ ኦክላንድ ሲቲን 6 ለ 0 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት አሸንፏል።
ትናንት ማምሻውን በኢንተር ኤንድ ኮ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ሊያንድሮ ባሬሮ ሁለት ግቦችን በጨዋታ እና አንጌል ዲማሪያ በተመሳሳይ ሁለት ጎሎችን በመለያ ምት አስቆጥረዋል።
ሬናቶ ሳንቼዝ እና ቫንጄሊስ ፓቭሌዲስ ቀሪዎቹን ግቦች ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።
የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያው አጋማሽ ጨዋታ ከተጠናቀቀ በኋላ ወደ ሜዳ ይመለሳሉ ተብሎ ሲጠበቅ በጠንካራ መብረቅ እና መጥፎ አየር ፀባይ ምክንያት ለሁለት ሰዓት ያህል ገደማ ተቋርጦ ነበር።
በፊፋ የክለቦች ዓለም ዋንጫ በአየር ፀባይ ምክንያት በጊዜያዊነት የተቋረጠ አራተኛ ጨዋታ ሆኗል።
ውጤቱን ተከትሎ ቤኔፊካ በአራት ነጥብ ምድብ ሶስትን መምራት ጀምሯል።
በምድቡ ሁለተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ኦክላንድ ሲቲ ከሲያትል ሳውንደርስ በመቀጠል ከውድድሩ የተሰናበተ ሁለተኛ ክለብ ሆኗል። የኒውዝላንዱ ክለብ በሁለቱ ጨዋታዎች 16 ግቦችን አስተናግዷል።