ሚድዋይፎች የእናቶችና የጨቅላ ህጻናት ጤና አጠባበቅን በማሻሻል ትልቅ ሚና እየተወጡ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሚድዋይፎች የእናቶችና የጨቅላ ህጻናት ጤና አጠባበቅን በማሻሻል ትልቅ ሚና እየተወጡ ነው
አዲስ አበባ፤ሰኔ 13/2017 (ኢዜአ)፦ሁሉን አቀፍ እና ደረጃውን የጠበቀ የእናቶች፣ የጨቅላ ህጻናትና የልጆች የጤና አገልግሎትን በማጠናከር ረገድ ሚድዋይፎች ትልቅ ሚና እየተወጡ መሆኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ የማኅበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወርቀሰሙ ማሞ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማህበር 34ኛውን የሚድዋይፎች ቀን "ሚድዋይፎች በቀውስ ወቅት ጉልህ ሚና አላቸው" በሚል መሪ ሀሳብ አክብሯል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ የማኅበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወርቀሰሙ ማሞ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ሁሉን አቀፍና ደረጃውን የጠበቀ የእናቶች፣ የጨቅላ ህጻናትና የልጆች ጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የሚድዋይፎች ሚና ጉልህ ነው።
ሚድዋይፎችን ጨምሮ የጤና ባለሙያዎች ሰውሰራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች በተከሰቱበት ወቅት እናቶችና ህጻናት ተገቢውን የጤና ክብካቤ እንዲያገኙ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች አባላት ከጤና ሚኒስቴር፣ ከክልል ጤና ቢሮዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት በመስራት ህዝብን ለማገልገል ያላቸውን ቁርጠኝነትና ጥንካሬ በተግባር አሳይተዋል ብለዋል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ሳህረላ አብዱላሂ፥ ሚድዋይፎች በችግር ጊዜ ጭምር የእናቶችን እና የልጆቻቸውን ጤና በመጠበቅ በወሊድ ምክንያት የሚከሰት ሞት ቅነሳ ላይ ጉልህ አስተዋፅኦ እያበረከቱ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
መንግስት ለጤናው ዘርፍ በሰጠው ትኩረት ብቁ ሙያተኞችን ማፍራት ላይ እየሰራ መሆኑን ገልጸው፥ ባለድርሻ አካላት ለጤናው ዘርፍ አገልግሎት መሻሻል የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
ሚድዋይፎች የእናቶችና የጨቅላ ህጻናትን ሞት ለመቀነስ ትልቅ ሚና እንዳላቸው የገለጹት የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሂንሰርሙ ባዩ፥ ሚናችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።