ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ሀገር በቀል እሳቤዎችን በማፍለቅ ለፓን አፍሪካኒዝም መጠናከር የመሪነት ሚናዋን እየተወጣች ነው-ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)

 

አዲስ አበባ፤ሰኔ 13/2017 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ሀገር በቀል እሳቤዎችን በማፍለቅ ለፓን አፍሪካኒዝም መጠናከር የመሪነት ሚናዋን እየተወጣች መሆኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) ገለጹ።

ተጠሪ ሚኒስትሩ ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ባዘጋጀው አርዳ የፖሊሲ ንግግር መድረክ ላይ "ፓን አፍሪካኒዝምን ማጠናከር" በሚል ርዕስ የመወያያ ጽሁፍ አቅርበዋል።


 

ለፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ ማንሰራራት መልካም ዕድሎችና ፈተናዎች መኖራቸውን በማብራሪያቸው ጠቅሰዋል።

አፍሪካውያን ኢትዮጵያ ዓድዋ ላይ በተቀዳጀችው ድል በመነሳሳት የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴን በማቀጣጠል የራሳቸውን ሉዓላዊነት ማወጅ መቻላቸውን አውስተዋል።

ከዚህም ባለፈ በፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ መሰረት የአፍሪካ ሕብረት እና ሌሎች ቀጣናዊና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ተቋማትን ማቋቋም ተችሏል ብለዋል።

ፓን አፍሪካኒዝም በ21ኛው ክፍለ ዘመን ተቋማዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፈተናዎች እንዳሉበት ገልጸው፥አፍሪካዊ ችግሮች በአፍሪካዊ እውቀትና ጥበብ እንዲፈቱ የተጀመረው ጥረት ተስፋ ሰጭ መሆኑን ተናግረዋል።

አህጉራዊና ቀጣናዊ ትብብርን የሚፈጥሩ ፕሮጀክቶችን ማስፋፋት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ለማጠናከርና ኢኮኖሚያዊ ትስስርን ለማፋጠን ያስችላል ብለዋል።


 

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፣ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና እንዲሁም ሌሎች ፕሮጀክቶች ለዚህ ዘመን የፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ ማደግ ገንቢ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘመናት ለፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ እድገት ታሪክ የማይዘነጋቸው ትላልቅ አሻራዎች አኑራለች፤ ዛሬም ቀጥላለች ነው ያሉት።

በተለይም ከለውጡ ወዲህ በመደመር እሳቤ የጀመረቻቸው ሀገር በቀል የሪፎርም ሥራዎች ለፓን አፍሪካኒዝም መጠናከርና ለአህጉራዊ ብልፅግና ትልቅ አስተዋጽኦ ያላቸው የተግባር ማሳያዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።

በአሁኑ ዘመን ድህነት፣ ኋላ ቀርነትና የእጅ አዙር የቅኝ አገዛዝ ተፅዕኖ የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ ፈተናዎች መሆናቸውን ጠቅሰው፥ የአፍሪካ የትምህርት ስርዓት በአፍሪካውያን ባህልና እሴት መቀረፅ አለበት ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም