በክልሉ ሰላምን ከማረጋገጥ ጎን ለጎን የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማጎልበት የሚያስችሉ ስራዎችን እውን ለማድረግ የአመራሩ ሚና ሊጠናከር ይገባል- ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ሰላምን ከማረጋገጥ ጎን ለጎን የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማጎልበት የሚያስችሉ ስራዎችን እውን ለማድረግ የአመራሩ ሚና ሊጠናከር ይገባል- ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ
ባህርዳር ፤ሰኔ 13/2017 (ኢዜአ) በአማራ ክልል ሰላምን ከማረጋገጥ ጎን ለጎን የህዝቡን ተጠቃሚነት ሊያረጋግጡ የሚችሉ ሁሉን አቀፍ የልማት ስራዎችን ለማከናወን የአመራሩ ሚና ሊጠናከር እንደሚገባ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ አስገነዘቡ።
"አርቆ ማየት አልቆ መስራት" በሚል መሪ ሃሳብ በክልሉ አሻጋሪ ዕድገትና የልማት ዕቅድ ላይ ለክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ለአንድ ሳምንት ሲሰጥ የቆየው ስልጠና ማምሻውን ተጠናቋል።
በስልጠናው ማጠቃለያ ላይ ተገኝተው ርዕሰ መስተዳድሩ እንደገለጹት ክልሉ ያለውን እምቅ የመልማት አቅም ወደ ስኬት በመቀየር ህዝቡን የልማቱ ተጠቃሚ ለማድረግ አመራሩ ከመቼውም ግዜ በላይ ተግቶ ሊሰራ ይገባል።
አመራሩ ተቋምን በእውቀት በመምራት ለ25 ዓመታት የሚተገበረው የክልሉ የልማት ዕቅድ ፍኖተ ካርታን ውጤታማ ለማድረግ ግንባር ቀደም ሚናውን መወጣት አለበት ብለዋል።
ይህም የክልሉን ልማት ለማፋጠን ጥራት ያለው ዕቅድ ከማውጣት ጀምሮ ዕቅዱን ለመፈፀም ብቁ ሆኖ መገኘት እንደሚገባም ጠቁመዋል።
ሃብት በመፍጠር ህዝቡን ተጠቃሚ ያደረገ ልማትን ማረጋገጥ በየደረጃው ካለው አመራር እንደሚጠበቅም እንዲሁ።
ዕቅዱም ኢትዮጵያ ከምትከተለው ብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚ ጋር ተጣጥሞ የታቀደ በመሆኑ በጀትን በአግባቡ ለልማት ማዋል እንደሚገባም ገልጸዋል።
ለዚህም ኃይል ከሚያባክኑ ትንንሽ ነገሮች ወጥተን በመተጋገዝ ዕቅዱን ለማሳካት ሁላችንም ግንባር ቀደም ሆነን ልንረባረብ ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።
በቀጣይም በየደረጃው የሚገኘው አመራር ዕቅዱን ወደ ራሱ ወስዶ የዘርፍና የተቋም ስትራቴጂክ ዕቅድን ከማዘጋጀት ጎን ለጎን የዘጠና ቀን ዕቅድ በማቀድ መተግበር እንደሚገባም ርዕሰ መስተዳድሩ አስገንዝበዋል።