ቀጥታ፡

የሃላላ ኬላ ሪዞርት ታሪካዊና ዘመናዊ የግንባታ ጥበብ የተሰናሰሉበት አስደናቂ የመስህብ መዳረሻ ነው - የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባላት

አዲስ አበባ፤ሰኔ 13/2017(ኢዜአ)፦የሃላላ ኬላ ሪዞርት ታሪካዊና ዘመናዊ የግንባታ ጥበብ የተሰናሰሉበት አስደናቂ የዓለም አቀፍ የመስህብ መዳረሻ መሆኑን የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባላት ገለጹ።

በሰኔ 11 ቀን 2017 ዓ.ም በቤተ-መንግስት ተገኝተው በሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር የተወያዩ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባላት የሃላላ ኬላ ሪዞርት ኢኮ-ቱሪዝምና የጊቤ-3 የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያን ጎብኝተዋል። 

በብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲያዊ ባህል ግንባታና የምርጫ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አሸብር ታደሠ (ዶ/ር)፥ በሀገራዊ ለውጡ ማግስት ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በቅርበት መስራት የሚቻልበት አዲስ የፖለቲካ ባህል እና ምኅዳር ተፈጥሯል ብለዋል። 


 

የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና እውን ለማድረግ በሚደረገው ጥረትም ሃላላ ኬላን ጨምሮ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በጥራትና በፍጥነት በማጠናቀቅ የኢኮኖሚ አቅም እንዲሆኑ መደረጉን ገልጸዋል። 

የሃላላ ኬላ ኢኮ-ቱሪዝም መዳረሻ ሪዞርትም ታሪክን በመጠበቅ ዘመናዊ የግንባታ ጥበብ የታከለበት ግዙፍ የልማት አቅም መሆኑን ተናግረዋል። 

የዳውሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዳዊት ገበየሁ በበኩላቸው፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት የተገነባው የሃላላ ኬላ ሪዞርት የተደበቀውን ታሪክ የገለጠ የመስህብ መዳረሻ ነው ብለዋል። 

ሪዞርቱም ለአካባቢው ወጣቶች የስራ ዕድል በመፍጠር ለዞኑ የቱሪዝም መነቃቃት ወርቃማ ዕድል በማምጣት የኢኮኖሚ አቅም እየፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል። 

በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ ገለታ ኃይሉ፥ ሃላላ ኬላ ሪዞርት በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ከተሞች ጸጋን በመለየት የቱሪዝም አቅም የሚሆኑ የልማት ስራዎችን ለመፍጠር ትምህርት የሚወሰድበት ነው ብለዋል። 


 

የአፋር ነፃ አውጪ ግንባር ፓርቲ ምክትል ሰብሳቢ ሀጂ እስማዔል መሀመድ፤ በአሁኑ ወቅት የተገነቡና በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኙ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከፍተኛ ድርሻ ይኖራቸዋል ብለዋል። 

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ዳውሮ ዞን በንጉስ ሃላላ ስያሜ የተገነባው ሪዞርትም ታሪካዊ ቦታዎችንና ቅርሶችን በመንከባከብና በመጠበቅ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ዕድል የፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል። 


 

በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የወጣቶች ክንፍ ምክትል ሰብሳቢና የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ የወጣቶች ክንፍ ኃላፊና የሥራ አስፈፃሚ አባል ጥጋቡ ደጀኔ፤ ሃላላ ኬላ ሪዞርት ታሪክና ዘመናዊ የግንባታ ጥበብ ተሰናስለው የተገለጡበት ዓለም አቀፍ ድንቅ የመስህብ መዳረሻ ስፍራ መሆኑን ገልጸዋል። 

የሃላላ ኬላ ሪዞርትም ለደቡብ ኢትዮጵያ ቀጣና የቱሪዝምና አገልግሎት ዘርፍ ልማት መነቃቃት ምቹ ሁኔታን እንደፈጠረም ተናግረዋል። 

በጋምቤላ ክልል የኢዜማ ምክትል መሪ ጋትቤል ቦል፥  ሃላላ ኬላ ሪዞርት ለአካባቢው የቱሪዝም ልማት ከፍተኛ አቅም መፍጠሩን ገልጸዋል። 


 

የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባላቱም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር በቤተ-መንግስት ያደረጉት ውይይት የሀገርን አንድነት በማስጠበቅ የጋራ ልማትና ሰላምን ለማጽናት ጉልህ ሚና እንዳለው አንስተዋል። 

በተለይም ከሀገራዊ ለውጡ ማግስት ጤናማና በሰላማዊ ፉክክር የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ምኅዳርን ለማስፋት እየተደረገ ለሚገኘው ስራ አጋዥ መሆኑን አብራርተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም